ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያዎች ችግር እንደገጠማቸው አኩሪ አተር አምራቾች ተናገሩ

152

ጎንደር፤ መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) የጥራት መጓደልና ብክነት እንዳይኖር ለማድረግ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያዎች ችግር እንደገጠማቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አኩሪ አተር አምራቾች ተናገሩ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ችግሩን ለመፍታት ለመውቂያዎቹ ግዢ የብድር አገልግሎት ለማሟላት እየሰራሁ ነው ብሏል።

በዞኑ ጠገዴ ወረዳ በአኩሪ አተር ልማት የተሰማሩት አቶ ዛይድ ወርቄ እንዳሉት፤ በመኸሩ ወቅት  በ42 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት አኩሪ አተር በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡቃያው እያበበ ያለውን የአኩሪ አተር ሰብል በጉልበት ታጭዶ የሚሰበሰብና የሚወቃ ከሆነ የምርት ጥራትና ብክነት እንደሚገጥማቸው ገልጸዋል።

በጠገዴ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አበበ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ምርቱ በሰው ጉልበት ሲሰበሰብ ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በመኸሩ ወቅት  በ60 ሄክታር መሬት ላይ አኩሪ አተር በመዝራት እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዛይድ፣ መንግስት የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያ እንዲያቀርብላቸው መፈለጋቸውን አስረድተዋል።

"በኩታ ገጠም እርሻ 10 ሄክታር መሬቴ ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ አኩሪ አተር አልምቻለሁ" ያሉት ደግሞ የምስራቅ በለሳ ወረዳ  አርሶ አደር ሞላ ታከለ ናቸው።

ከዚህ ቀደም አኩሪ አተርን ማምረት በአካባቢው ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በምርት አሰባሰብ ላይ ችግር እየገጠማቸው በመሆኑ መንግስት ብድር በማመቻቸት ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያ እንዲያቀርብላቸው አመልክተዋል።

በመኸሩ እርሻ በወረዳው በባለሀብቶችና አርሶአደሮች 4ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ አኩሪ አተር መልማቱን የገለጹት ደግሞ የጠገዴ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘውዴ ጀጃው ናቸው።

"በአሁኑ ወቅት ሰብሉን ከአረምና ተባይ በመከላከል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ በመሆናቸው ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

አቶ ዘውዴ እንዳሉት ፤ በአኩሪ አተር ከለማው ሰበል ከ120ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

ጥራቱን የጠበቀ ምርት አምርቶ ወደ ውጭ ለመላክ እንዲቻል አምራቾቹ የፈለጉትን ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያ  እንዲቀርብላቸው ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸው ነው የገለጹት።

የማዕከላዊ ጎንደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጋ ይስማው በበኩላቸው፤ በዞኑ የአየር ንብረታቸውና ስነ ምህዳራቸው ተስማሚ በሆኑ አራት ወረዳዎች ከ16ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በአኩሪ አተር ለምቷል ነው ያሉት።

ከለማው መሬት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ ይህን በሰው ጉልበት ለመሰብሰብ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ፤ የአምራቾቹ የፈለጉትን መሳሪያ ተገቢ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ብድር ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።  

አምራቾቹ የመሳሪያውን  ዋጋ 30 በመቶ አቅርበው ቀሪውን 70 በመቶ ከባንክ ብድር የሚያገኙበት አሰራር መሆኑንም አስረድተዋል።

ሆኖም በሀገሪቱ በተፈጠረ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የአኩሪ አተር መሰብሰቢያ መሳሪዎችን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት አለመቻሉን ነው ያመለከቱት።

በተያዘው በጀት ዓመት በልዩ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ለስንዴ፣ ለጤፍና በቆሎ ምርት መሰብሰቢያ አገልግሎት የሚውሉ 20 ኮምባይነሮች ተገዝተው መግባታቸውን ጠቁመው፣ "በየዓመቱ ተጨማሪ 100 የሚጠጉ ኮምባይነሮችንም ከሌሎች አካባቢዎች በማስመጣት ምርት እንዲሰበሰብ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

በአማራ ክልል የግብርና ምርት ማቀናበሪያ ኢንዱስትሪዎችን የግብአት ፍላጎት ለማሟላት በ2013/14 ምርት ዘመን 90ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር እንዲለማ ተደርጓል።

ከለማው መሬትም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም