የውጭ ሃይሎች በሱዳን ጉዳይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ለኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት መሻከር ምክንያት ሆኗል

87

መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የውጭ ሃይሎች በሱዳን ውስጣዊ ጉዳዮች የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ለኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት መሻከር ምክንያት መሆኑን የሱዳን ፖለቲካ ተንታኞች ተናገሩ።

ኢትዮጵያና ሱዳን ዘመናትን የተሻገር ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ መጥቷል።

በተለይ የወቅቱ የሱዳን መንግስት በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ደህንነት ላይ ከንቱና ያልተረጋገጡ ሰበቦችን በመደርደር የሶስትዮሸ ድርድሩን ማስተጓጎሉን ቀጥሏል።

በተጨማሪ የወቅቱ የሱዳን መንግስት በሁለቱ አገራት የድንበር አለመግባባቶቸን ለመፍታት የተቋቋመውን የጋራ የድንበር ኮሚሽኖች ወደ ጎን በመተውና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በሃይል ጥሶ በመግባት ወረራ ፈጽሟል።

ይህም የሁለቱ አገራት የቆዬ መልካም ግንኙነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመሻከሩ ሰበብ ሆኗል።

ሱዳናዊያን የፖለቲካ ተንታኞች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የውጭ ሃይሎች በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ላይ እያደረጉ ያሉት ጣልቃ-ገብነት ለሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ግንኙንት መሻከር በምክንያትነት አንስተዋል።

የፖለቲካ ተንታኙ ሐሊ ያህያ በርካታ የውጭ ሃይሎች በአፍሪካ ቀንድ የሚያልሙትን ግላዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በሱዳን ውስጣዊ ጉዳይ ገብተው እየፈተፈቱ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቧንም አስታውሰዋል።

ምንም እንኳ በርካታ የሱዳን ምሁራንና ፖለቲከኞች የግድቡ ግንባታ ለሱዳን ህዝብ አውንታዊ ሚና እንደሚኖረው ቢመሰክሩም፤ ዳሩ ግን የሱዳን መንግስት በተቃራኒው በአፍራሽ ተግባራት ላይ ተጠምዷል ብለዋል።

በኢትዮ-ሱዳን መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፈታት እንደሚቻልም ነው ያነሱት።

የውጭ ኃይሎች ግን የጋራ የጥቅምና ትስስር ያላቸውን ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚጎዳ መልኩ ጉዳዩ በኅይል እንዲፈታ እንደሚሹ ተናግረዋል።

የውጭ ሃይሎች በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ-ገብነት ሱዳናዊያን ልሂቃን በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት እንዳይፈቱ እክል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

ሌላው ጋዜጠኛና የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ አባስ መሃመድ ሳላህ በበኩላቸው የአፍሪካ አገራት በተለያዩ ምክንያቶች ለውጭ ሃይሎች ጫና እና ጣልቃገበንት የተጋለጡ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የማያግባቧቸው ጉዳዮችን በውይይትና በድርድር እንዲሁም በፖለቲካዊ መግባባትና ጥበብ መፍታት እንዳለባቸው መክረዋል።

ሁለቱ ሀገሮች አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሏቸው የሚገልጹት አባስ መሐመድ፤ በመሆኑም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም