የምዕራባውያን መጽሐፍት ሽፋኖች ምስሎች ስለ አፍሪካ ምን ይነግሩናል?

129

መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) በምዕራባውያን መጽሐፍት የሽፋን ገጾች ምስሎች ላይ አፍሪካ በምን መልኩ እየተሳለች ነው? ምስሎቹ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚቀርጹት ምን ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

የምዕራባዊያን መጽሀፍት ከጭብጦቻቸው በላይ በሽፋን ገጽ ምስሎች በርካታ ጉዳዮችን እንደሚያመለክቱ ብዙዎች ይስማማሉ። ሀሳባቸውን በምስሎቹ አማካኝነት አሉታዊ አስተሳሰቦችን ለማስረጽ ይጥራሉ።

የ'ፀሓይ አሳታሚ' ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ለ'አለ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት' ተማሪዎች "የመፅሓፍት ሽፋን ገጾች ፖለቲካና እውቀት የማሰራጨት ሒደት" በሚል ርዕስ ያደረጉት ገለጻ የሚያመለክተው ሀሳብም ይሄንኑ የሚያጸና ነው።

አቶ ኤሊያስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዓለም ላይ ያለውን እውነታ ከቀየሩት ክስተቶች መካከል "የመጽሓፍት ህትመት ነው ተብሎ ይታሰባል"።

ከዚሁ ክስተት በኋላ የምዕራባውያን ደራስያን ለዘመናት አፍሪካን ለራሳቸው በሚመች መልኩ ቀርጸው ለሽፋን ገጻቸው ሲጠቀሙ እንደነበር ያትያሉ።

ምዕራባውያኑ በቅዱሳት መጽሓፍት ጭምር ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ መልዕክቶችን ለራሳቸው በሚመች መልኩ እየተረጎሙ የጥቁሮችን 'አናሳነት' መግለጻቸውን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ አህጉርን የተመለከቱ መጽህፍት የሽፋን ገጻቸው ምስሎች 'የግራር ዛፍና ልትጠልቅ ያለች ፀሓይ' የብዙ መጽሃፍት የሽፋን ገጾች ምስሎች እንደሆኑ ይገልጻሉ።

ምዕራባውያኑን የተመለኩ መፅሓፍት ሲታተሙ ግን የሽፋን ገጻቸው አማላይና ሳቢ በሆነ መልኩ የታቀኙ ናቸውም ይላሉ።

ይህና ሌሎች ምክንያቶች ተዳምረው አፍሪካውያን ምዕራባውያኑ የሰለጠኑ እንደሆኑ በማሰብ "የራሳቸውን ማንነት ትተው ለምዕራባውያኑ ሁለንተናዊ ህይወት ጉጉህ ሆኑ" ብለዋል።

ሁኔታው አፍሪካ ተስፋ የሌላት፤ ጨለምተኞች የሚኖሩባት አህጉር ሆና እንድትታይ አድርጓል፣ ይህም አፍሪካውያን ጸሓፊዎች ጭምር ትክክል እንደሆነ እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

በዚህ ስልታዊና የረቀቀ መንገድ ሲፈጸም የቆየው የምዕራባውያን ደባና ሸፍጥ ''ታሪካችንን እንዳናውቅ፣ ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት አድርጎናል'' ባይ ናቸው።

እንደ ምሳሌ ካነሷቸው መፅሓፍቶች መካከል 'Hearts of Darkness' የተባለው መፅሓፍ የሽፋን ገጹ ላይ አፍሪካ አስቀያሚ ሆና ከተሳለችባቸው መካከል አንዱ ነው ።

መሰል የመፅሓፍት ሽፋን ገጾች ምስሎች አፍሪካውያን በጥቅሉ "'ፈረንጅ አምላኪ' እንዲሆኑና የራሳቸውን ማንነትና ስብዕና እንዲክዱ እድል ፈጥሯል" ይላሉ።

ይህው አካሄድ አፍሪካውያንም በአገራቸው ያሉ የታወቁ ስፍራዎች ላይ 'ነጭ ካላዩ' ስፍራዎቹን እንዳይጎበኙ ጭምር ይሆናሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም እንደማንኛውም አፍሪካዊ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፍን በመሆናችን "ቀደምት እውቀታችን ወደ ውጪዎቹ ሊደርስ አልቻለም" በማለት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ጠላቶችም በዚህ ወቅት በትክክለኛ መልካቸው እየተገለጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁኔታን በአግባቡ መረዳት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በዋናነት ከዚህ "ችግር ለመውጣት ትልቁ መፍትሄ 'ኢትዮጵያዊ የሆነ ትምህርት' ማስፋፋት ነው" ብለዋል አቶ ኤሊያስ።

የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤቱም ቢሆን "በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ነገሮችን መቀየር እንደሚችል አውቆ መስራት አለበት" ሲሉም አንስተዋል።

የ'አለ' የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አገኘሁ አሰግድ በበኩላቸው፤ "እንደ ኤሊያስ ያሉ አገር ወዳድ ዜጎች ብዙ ነገር መቀየር ይችላሉ" ብለዋል።

የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤቱ ለስድሳ ዓመታት ገደማ የተሰሩ የስነ-ጥበብ ስራዎች የተከማቹበት እንደመሆኑ ይህ መልካም እድል መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም