ዝናቡ ለመኸር እርሻ ዝግጅት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ገለፁ

64
ወልዲያ ግንቦት 8/2010 በሰሜን ወሎ ዞን እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ ለመኸር እርሻ ዝግጅት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ ዝናቡን በመጠቀም 222 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለመኸር ልማት መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር ጌታቸው አበራ በሰጡት አስተያየት በመጋቢትና ሚያዝያ የጣለው የበልግ ዝናብ ለመኸር ማሳ ዝግጅትና ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ የወቅቱን ዝናብ በመጠቀም ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን አርሰው ቀድሞ በሚዘራው የማሽላ ሰብል ሸፍነዋል፡፡ ቀሪውን ደግሞ አርሰውና አለስልሰው ለጤፍ ዘር ማዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡ በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ 03 ነዋሪ አርሶ አደር ተፈራ ውዱ በበኩላቸው የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ የጣለ በመሆኑ ይህንኑ ተጠቅመው አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማሽላ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ የቀበሌ 06 ነዋሪ አርሶ አደር አሊ ሰይድም ዝናቡን ተጠቅመው ለዘር ካዘጋጁት መሬት አንድ ሄክታር ተኩሉን ማሽላ በብተና መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዝናቡ ከማሳ ዝግጅት በተጨማሪ ለእንስሳት የተሻለ የሳር ግጦሽ በማስገኘት እየጠቀማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ግብርና መምሪያ የአዝርእት ባለሙያ አቶ አሸናፊ ልዑልሰገድ እንደገለፁት ደግሞ በዞኑ የበልግ ልማት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ዝናቡ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ዘንቧል፡፡ ዝናቡን በመጠቀምም ለመኸር ልማት የሚውል ከ222ሺ ሄክታር በላይ ማሳ ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም አጠቃላይ በመኸር ወቅት ለማልማት በእቅድ ከተያዘው 239 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ውስጥ 93 በመቶ የሚሆነውን ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ራያ ቆቦ፣ ጉባላፍቶና ሀብሩ ዝናብ አጠርና ቆላማ ወረዳዎች የወቅቱን ዝናብ በመጠቀም ታርሶ ለዘር ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ 13ሺህ 300 ሄክታር መሬት ቀድሞ በሚዘራው የማሽላ ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል። ከተዘራው ውስጥም 509 ሄክታር በመስመር መዘራቱን ተናግረዋል፡፡ የበልጉ ዝናብ ለመኸሩ ማሳ ዝግጅት ከፈጠረው መቹ ሁኔታ በተጨማሪ ከ28ሺ ሄክታር በላይ የበልግ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት እንደተቻለም አቶ አሸናፊ አክለው አስታውቀዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን በመጭው የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት ከ6 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም