በከምባታ ጠምባሮ ዞን እየተከናወነ ያለው የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት ነው--አቶ ኡመር ሁሴን

137

ሀዋሳ፤ መስከረም 09/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን እየተከናወነ ያለው የእንስሳት ሀብታና መኖ ልማት እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ከክልሎች የሴክተርና ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎች ጋር በመሆን በከምባታ ጠምባሮ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ የወተት ላሞች ዝርያ ማሻሻያ ሥራዎችና የእንስሳት መኖ ልማት እንቅሰቃሴን በመስክ ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት  አቶ ኡመር እንዳሉት፤ የአካባቢው አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት የሚሰጡ ጥቂት የወተት ላሞችን በመያዝና በጠባብ መሬት ላይ የእንስሳት መኖ በማልማት የተሻለ ገቢ ማመንጨት በመቻላቸው እውቅና ይገባቸዋል።

እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት ተግባር ማከናወናቸውንና ይህም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊሰፋ የሚገባው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሀብት ውስጥ የተሻሻለ ዝርያ ሽፋን ከሶስት በመቶ ያነሰ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በከምባታ ጠምባሮ ዞን 31 በመቶ ማድረስ መቻሉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም በዚህ ልክ ተጠቃሚ አይደለንም ነው ያሉት።

ብዛት ላይ ከማተኮር ይልቅ ጥራት ያላቸውን የተሻሻለ ዝርያ በመያዝና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ሀገሪቱ ከዘርፉ  ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ መስራት ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ።

የዞኑ አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን ወተት እሴት ጨምረው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአካባቢው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲኖር ሚንስቴሩ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው፤ የዞኑን የእንስሳትና መኖ ልማት ሥራ በሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ቢሮው 45 ሺህ ዶዝ የዝርያ ማሻሻያ እና "ማድሪያ ሆርሞን" ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን አስረድተዋል።

ከ340 በላይ ለሚሆኑ አዳቃይ ባለሙያዎችም የክህሎት ሥልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

ከግብርና ሚኒስቴር በተገኘ ድጋፍ 26 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን በመግዛት እያሰራጨን እንገኛለን ብለዋል።

 በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት በተከናወነው የዝርያ ማሻሻል ሥራ ከ16 ሺህ በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ጥጆች መወለዳቸውን የገለጹት ደግሞ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ አጪሶ ናቸው።

ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይም የእንስሳት መኖን ማልማት ተችሏል ብለዋል።

በተለይ የወተት ልማት ኩታ ገጠም ወረዳዎችን በመለየት ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ   ሴት አርሶ አደር አረጋሽ አባይነህ በሰጡት አስተያየት፤ በአንድ የወተት ላም የጀመሩትን ሥራ አሁን ላይ ሶስት የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች አሉኝ ብለዋል።

ለነዚህ ላሞች የሚሆን መኖ አንድ ሄክታር በሚጠጋ መሬታቸው ላይ እያለሙ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ገቢዬ ከቀለብና የዕለት ወጪ አያልፍም ነበረ የሚሉት አርሶ አደሯ፤ አሁን ላይ ከወጪ ቀሪ ከወተትና የወተት ተዋፅኦ የሚያገኙት ወርሀዊ ገቢ እስከ 25 ሺህ ብር መድረሱን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ፋኖስ ኤርሱሞ በበኩላቸው፤ አሁን ካሏቸው ሶስት የወተት ላሞች በቀን እስከ 75 ሊትር ወተት እንደሚያገኙ፣ ከሽያጩም በወር እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ የተጣራ ገቢ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአካባቢው የወተት ምርት  በቋሚነት የሚያስረክቡበት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ቢኖር ከዚህም የተሻለ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው አርሶ አደር ፋኖስ የተናገሩት።

በተጨማሪም በስልጤ ዞን እየተከናወነ ያለው የኩታ ገጠም ሰብል ልማት ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም