የክልሉ ህዝብ የሽብር ቡድን የጥፋት ተላላኪዎችን በመመከት የጀመረውን ልማት አጠናክረን መቀጠል አለበት -- አቶ ኡሞድ ኡጀሉ

77

ጋምቤላ፤ መስከረም 09/2014 (ኢዜአ) የክልሉ ህዝብ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን የጥፋት ተላላኪዎችን በመመከት የጀመረውን የልማት ተሳትፎና ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ አሳሰቡ።

በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ በህዝብ ተሳትፎ ከ5 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ የተገነባ የወረዳው አስተዳደረ ህንፃ ዛሬ ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ፤ ባለፉት ዓመታት ክልሉ በተለይም የኢታንግ ልዩ ወረዳ የሽብር ቡድኑ በሚፈጥረው የግጭት ሴራ ህዝቡ በሰላምና በልማት አጦት ሲሰቃይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሆኖም  ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ክልሉ በተለይ የኢታንግ ልዩ ወረዳ ከግጭት ቀጠና ተላቃ ህዝብ አንድነቱን በማስጠበቅ ፊቱን ወደ ልማት ማዞሩን ተናግረዋል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው በዕለቱ በህዝብ ተሳትፎ የተገነባው የወረዳው የአስተዳደር ህንፃ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ድርጊቱ ያልተቆጠበውን የሽብር ቡድኑን የጥፋት  ተላላኪዎችን ነቅቶ በመጠበቅና በመመከት የወረዳውን ብሎም የክልሉ ልማት ለማፋጠን ህዝቡ የጀመረውን የልማት ተሳትፎ አጠናከሮ ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት በአዲስ ዓመት በተለይም የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሪጀክቶችን ፍፃሜያቸውን እንዲያገኙ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አቶ ኡሞድ አስታውቀዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት የወረዳው ብሎም የክልሉ ሰላም ሲነጋ የቆየው በአሸባሪ የህወሓት ሴራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወረዳው አስተዳደሪ አቶ ኦኬሎ ኡቦንግ ናቸው ።

ይሁን እንጂ ከለወጡ ወዲህ ቀደም ሲል በወረዳው የነበረው ግጭት መወገዱን ያስታወሱት  የወረዳ አስተዳደሪ፤ አሁን ላይ የወረዳው ህዝብ ሰላሙንና አንድነቱን በማስጠበቅ ወደ ልማት መግባቱን ተናግረዋል።

በህዝብ ተሳትፎ ከአምስት ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ ተገንበቶ የተመረቀው የአስተዳደር ህንፃ  የህዝቡ የልማት ተነሳሽነት ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በምርቃው ስነ- ስርዓት  የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በወረዳው የተጀመሩ የልማት ስራዎችንም ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም