የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የመጀመሪያ ልኡካን ጅግጅጋ ከተማ ገቡ

81
ጅግጅጋ ነሀሴ 9/2010 ሶስት አባላትን የያዘው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር /ኦብነግ/ የወጣቶች ክንፍ ተወካዮች የልኡካን ቡድን በጀግጅጋ ጋራድ ዊልዋል አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደረገለት። ቡድኑን የመሩት የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የወጣቶች አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሻፊ ሼህ አብዲ ትላንት ማምሻውን ሲገቡ እንደገለጹት "በጅግጅጋ ከተማ የተገኘንበትት ዋነኛ ዓላማ ግንባሩ በቀጣይ በከተማዋ ለሚያዘጋጀው ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ነው" ብለዋል፡፡ ግንባሩ ከሁለት ዓስርት ዓመታት በኋላ በጅግጅጋ የሚያደርገው ጉባኤ ላይ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። በልኡካን ቡድኑ አቀባባል ላይ ያገኘነው ወጣት ሱልጣን ከውመዳ እንደተናገረው ግንባሩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብሎ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ መወሰኑ ለክልሉ መረጋጋት አውነታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ግንባሩ በከልሉ ያለው የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ አማራጭ ፓርቲ አንደሚሆንም ያለውን እምነት ገልጿል። ዜጎች የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ መብታቸው በህገ-መንግስቱ እንደተደነገገ ያሰታወሰው ወጣቱ፤ይህን በመጠቀም ለሀገራቸው የፖለቲካ እድገት መስራት አንዳለባቸው ተናግሯል። ግንባሩ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ለመፍታት የሚያግዝ ተግባራት ላይ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም