በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለው ዛቻ እና ዘመቻ በኢትዮጵያዊያን አንድነት ይመክናል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለው ዛቻ እና ዘመቻ በኢትዮጵያዊያን አንድነት ይመክናል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለውን ዛቻና ዘመቻ ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብና መንፈስ አገር ለመታደግ ሊቆሙ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ካቢኔ አባላት ተናገሩ።
የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተመንግስት ንቅናቄን የተቀላቀሉት የካቢኔ አባላቱ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ለወዳጅነት መርህና ለዲፕሎማሲ ትርጉም የሚሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በተከፈተው የክህደት ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከዳር በአንድነት ቆመዋል ብለዋል።
ወቅቱ ኢትዮጵያዊያን የአገር አለኝታነታቸውን ለማረጋገጥ በጋራ የተመሙበት፤ እንደ አድዋ ለነፃነት በተደረጉ ጦርነቶች የነበረው አንድነት የተደገመበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ዛቻና ዘመቻ ለማምከን ሁሉም ለአገሩ ሕልውና በጋራ በመቆም ማምከን እንዳለበትም አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው በሽብርተኛው ኃይል የተፈፀመው ጥቃት በአገሪቷ ሉዓላዊነትና በሕዝቡ ደህንነት ላይ የተቃጣ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ ጥቃቱን ለመመከት እየተረባረበና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነታውን ተገንዝቦ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ባልተገባ መንገድ ስትጠቃ ቆማ የመመልከት ታሪክ የላትም ያሉት አቶ መለሰ ይህ ተግባር በአሁኑም በቀጣዩ ትውልድም የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ጥቃቱ አገር ከመውረርና ማስወረር ተለይቶ የማይታይ በመሆኑ ይህን ጥቃት ለመቀልበስ ሁሉም በአንድነት መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ማዕቀብና እርምጃ የአፍሪካ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ ናቸው።
የመዲናዋ ወጣቶችና በጎፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው ወቅቱ የሕዝቦችን አንድነት የሚጠይቅ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አመላክተዋል።