በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በአገር ቤት ለማክበር አዲስ አበባ መግባት ጀመሩ

50
አዲስ አበባ ነሃሴ 9/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በአገር ቤት እንዲያከብሩ ባደረጉት ግብዣ መሠረት አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል። ዛሬ ማለዳ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በለንደንና በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኢትዮጵያ የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍጹም አረጋና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስለ አገራቸው ብዙ መልካም ዜናዎች ሲሰሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተፈጠረው ለውጥና ሰላም በውጭ ሆነው መስማታቸው ያለምንም ስጋትና ፍርሃት አዲሱን ዓመት በአገራቸው ለማሳለፍ መምጣታቸውን ተናግረዋል። በተለይም መንግስት ለረጅም ዓመታት በውጭ አገር የቆዩ ዜጎች ለአገራቸው እንዲበቁ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ትልቅ ነገር እንደሆነም ገልጸዋል። በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያኑን ወደ አገራቸው መጥተው አዲሱን ዓመት በአገራቸው እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኢትዮጵያ የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍጹም አረጋ በበኩላቸው፤ ዛሬ ወደ አገራቸው የገቡት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአውሮፕላን ትኬት ቅናሽ ተጠቃሚ ባይሆኑም በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ቅናሽ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል። በቀጣይም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሲገቡ አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ዜጎች በአዲሱ የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር እሳቤ መሠረት ተቀራርበው ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ተሳትፎ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ''በዚህ 45 ቀናት ውስጥ በርካታ በዓላት የሚደረጉበት በመሆኑ በአዲሱ የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር እሳቤ መሰረት ህዝቡ እርስ በርሱ ተቀራርቦ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ተሳትፎ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት እንዲሁም ለምሳሌ የምናከብራቸው በዓላት፣ አረፋ አለ፣ ኢዳል አዳሃ አለ፣ ቡሄ በዓል አለ፣ አሻንዳ አለ፣ የአዲስ አመት፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓል አለ። የመስቀል በዓል ራሱ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የሃዲያ መስቀል እያሉ በድምቀት የሚያከብሩበት አለ። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ በዓላት ከህዝቡ ጋር እያከበሩ ለኢኮኖሚውምና ለቱሪዝሙ እድገትም  የበኩላቸውን ይወጣሉ።'' ብለዋል  በተጨማሪም ሕዝቡ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መልኩ በልዩ ሁኔታ ተቀብሎ እንዲያስተናግዳቸው ጥሪ አቅርበዋል።  '' ሰው በቅሬታና በኩርፊያ ውስጥ ስለነበረ አገሩን ማየት ያልቻለ በጣም ከፍተኛ ህዝብ አለ፤በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት ማየት እንደተቻለው አንዳንዶቹ አንድም ቀን ኤምባሲ ሄደው የማያውቁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የእነሱ መሆኑን እንኳን የማያውቁ ሰዎች ከሌሎች ኢዮጵያውያን ጋር ተራርቀው የነበሩ በሚገርም ፍቅር በሚገርም ናፍቆት ወደ አገራቸው ለመምጣት ከፍተኛ ጉጉት እንዳያሳዩ ማየት ይቻላል። ስለዚህ የሚመጣው ሰው ቁጥር ከፍተኛ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። አጠቃላይ ወደ 10 ሺህ የሚሆን መኝታ አለን ይሄ ሞልቶ ቀሪው ወደ ቤተሰብ እንደሚሄድም እንጠብቃለን ሰው በሁሉም መልኩ በልዩ ሁኔታ ተቀብሎ በመልካም መስተንግዶ እንዲንከባከባቸውና እነሱም ደግሞ ከወገናቸው ጋራ የማይረሳ ትዝታ እንዲያሳልፉ እንመኛለን።''ብለዋል አቶ ፍፁም አረጋ ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያዊያን ለአዲስ ዓመት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም