አቶ ወርቁ አይተነው ደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከቱ

132

ደሴ፣ መስከረም 8/2014 ( ኢዜአ ) ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ለደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ማጠናከሪያ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው እንደገለጹት የደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን ለማጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

"ቡድኑ አሁን ካለበት ከፍተኛ ሊግ ወደ ብሔራዊ ሊግ እንዲያድግ በገንዘብና በሌላም ማበረታታትና መደገፍ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ለእግር ኳስ ቡድኑ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ የቡድኑን አቅም ለማሳደግ በማሰብ ላደረጉት ድጋፉም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

"ባለሃብቱ አቶ ወርቁ አይተነው በበኩላቸው ቡድኑን ለማጠናከር የተደረገው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

ከእግር ኳስ ቡድኑ በተጨማሪ በወሎ ግንባር በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለተፈናቀሉ ዜጎችም 25 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች እስከ 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

የደሴ እግር ኳስ ቡድን ባለፈው ዓመት ከከፍተኛ ሊጉ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡

ባለሃብቱ በደሴ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ ባህልና ኪነት ቡድኖችም 500 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም