በሶማሌ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከት የራሳቸው ያልሆነ ንብረት የያዙ ግለሰቦች በአፋጣኝ እንዲመልሱ ጥሪ ቀረበ

98
ጅግጅጋ ነሀሴ 9/2010 የራሳቸው ያልሆነ ንብረት የያዙ ግለሰቦች የተቀመጠውን የምህረት ጊዜ ተጠቅመው በአፋጣኝ እንዲመልሱ የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ሼህ አብድረህማን ሃሰን ጥሪ አቀረቡ። ሼህ አብድረህማን ከሰሞኑ በክልሉ ተከስቶ የነበረው ሁከትና ዝርፊያ በእስልምና አስተምህሮ የተወገዘ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል። በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከት መጠነ ሰፊ ዝርፊያ የተካሄደ ሲሆን የተዘረፉ ንብረቶችን የሚያስመልስና የሃይማኖት አባቶች የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራውን ጀምሯል። ኮሚቴው እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ማንኛውም ግለሰብ በእጁ የያዘውን የራሱ ያልሆነ ንብረት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ቢሮዎች እንዲያስረክብም የምህረት ጊዜ ገደብ አስቀምጧል። ከተጠቀሰው ቀን በኋላ የጸጥታ አካላት ህጋዊ አሰራሮችን ተከትለው የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ እንደሚሰሩም አስታውቋል። የኮሜቴው አባል የሆኑት የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ሼህ አብድረህማን ሃሰን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ እንደገለጹት በሰው ላይ ጥቃት ማድረስና የራስ ያልሆነን ንብረት መዝረፍ በእስልምና በጥብቅ የተከለከለ ተግባር ነው። ከሰሞኑ ባልተለመደ መልኩ በክልሉ የታዩ  ህገወጥ ተግባራት ውጉዝ መሆናቸውን የተናገሩት ሼሁ የራሳቸው ያልሆነ ንብረት በእጃቸው የያዙ ግለሰቦች ሳይውሉ ሳያድሩ እንዲመልሱ አስገንዝበዋል። በአቅራቢያቸው የጸጥታ ቢሮዎችን የማያገኙ አካላት በየአካባቢያቸው ለሚገኙ መስጊዶች መመለስ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። ንብረቶቻቸውን የተዘረፉ ወገኖች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደገጠማቸው የተናገሩት ሼህ አብድረህማን ንብረታቸውን በአፋጣኝ በበመለስ 'ከችግር እንዲወጡ የማገዝ ግዴታ አለብን' ነው ያሉት። ይህን ሳያደርጉ ቀርቶ የራስ ያልሆነን ንብረት መጠቀም ግን በምድራዊም ሆነ በኋለኛው ህይወት ቅጣቱ የከፋ እንደሚሆን መክረዋል። በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን ድንጋጤ ለማረጋጋት የሃይማኖት አባቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግተው እንዲሰሩም ሼህ አብድረህማን ጥሪ አቅርበዋል። በሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ሰላማቸው ደፍርሶ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ ወደመረጋጋት እየተመለሱ ሲሆን ሰላሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠልም ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ህዝባዊ ጉባዔ ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም