የአሸባሪው ህወሓት ግፍ እና በደል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን

64

ሐረር ፤ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለማስገንዘብ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ የሐረሪ ክልል ወጣቶች ተናገሩ።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት" ዘመቻ በሐረሪ ክልል  ዛሬ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ በዚህም ወጣቶች፤  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና  የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሐመድ ተሳትፈዋል።

በዚህ ወቅት ወጣቶቹ አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው የማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት።

የሐረሪ ክልል ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት ሸሪፍ ሙሜ እንዳለው፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በአሁኑ ወቅት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

 "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት" ዘመቻ  ዓላማም ኢትዮዽያ ለሰላም ያላትን ጽኑ አቋም ለሌላው ዓለም ለማስረዳት መሆኑን ገልጾ፣ በንቅናቄው ከ10ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ መታቀዱን አስታውቋል።

የክልሉ ወጣቶች በንቃት በመሳተፍ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል እንዲያውቀው የማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ጥሪ አድርጓል።

"አሜሪካ እና ኢትዮዽያ የዘመናት ወዳጆች እንደሆኑና ህወሓት በፈጠረው የተሳሳተ መረጃ በሀገራቱ መካከል ልዩነት እንዳይፈጥር እኛ ወጣቶች ትክክለኛውን መረጃ የማሳወቅ ግዴታ አለብን" ያለችው ደግሞ  ወጣት ሲትራ በሓር ናት።

በዚህም የጥፋት ቡድኑ በዜጎች በተለይ ደግሞ በሴቶች እና ህጻናት ላይ እየፈጸመ ያለውን የጥፋት ተግባር ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ የማድረግ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መነሳሳታቸውን ተናግራለች።

ወጣት ሙስጠፋ ኤልያስ በበኩሉ፤በዘመቻው  ወራሪው ቡድን በሀገሪቱ የጅምላ ግድያ፣ ህጻናትንና ሴቶችን የመድፈር እንዲሁም ህጻናትን በግዳጅ ጦር ሜዳ እያሰለፈ ስለመሆኑ እንዲሁም የኢትዮዽያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በሃላፊነት ስሜት እንደሚጥር ገልጿል።

የአሜሪካ መንግስት በተለይ እውነታውን በመረዳት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቋል።

ወጣቱም የሀገርን ገጽታ ለመገንባት እያደረገ ያለውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስተባበር የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት" ዘመቻ በሐረሪ ክልል እስከ መስከረም 15/2014 ዓ.ም. እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም