በሀገሪቱ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ተጨማሪ ስንዴ ይመረታል –ግብርና ሚኒስቴር

212

ሀዋሳ፤ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ ተጨማሪ ስንዴ ለማምረት እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2013 የግብርና ሥራ አፈፃፀምና የተያዘው የስራ ዘመን  አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል ፡፡

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንደተናገሩት፤  ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ አምርቶ ለመተካት በተለይ ከአምና ጀምሮ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

ስራው  ከክልል ክልል የአፈፃፀም ልዩነት ቢኖረውም አበረታች ውጤት የተገኘበት ነው ያሉት።

በበጋ መስኖ ብቻ በ400 ሺህ ሄክታር ፤  በበልግና ክረምት ደግሞ 300 ሺህ  ሄክታር ላይ ስንዴ  እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡

በዚህም  እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ ስንዴ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ሙሉ በሙሉ ለመተካት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሥራዎች በቅንጅት ከተመሩ የስንዴ ምርትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የመተካቱ ዕቅድ በአንድ ዓመት ውስጥ መሳካት የሚችል ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩን ከገበያው ጋር የሚያስተሳስር የፋይናንስና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ አሰራሮች መዘርጋት እንዳለባቸው ጠቆመዋል።

በበልግ ወቅት ባጋጠመው የዝናብ እጥረት፣ በጸጥታ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ምርት ያልተመረተባቸው ማሳዎች በመኖራቸው በዚህ ሳቢያ ሊከሰት የሚችልን የምርት እጥረት  ለማካካስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 በበልግና መኸር የሚከናወኑት የግብርና ሥራዎች በዝናብ ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው በክልሉ ለመስኖ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ናቸው።

”የግብርና ሥራዎቻችንን ከዝናብ ጥገኝነት አላቀን በመስኖ ወደ ሚታገዝ አሰራር እየቀየርን ነው” ያሉት አቶ ጌቱ ፤  600 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ይሰራል ነው ያሉት።

የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በመስኖ ሊለሙ የሚችሉባቸውን ቦታዎች በመለየት በኩታ ገጠም  የማልማት ሥራ  ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል ፡፡

የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፤  በክልሉ በአምናው የምርት ዘመን በቡና፣ ቦሎቄና ሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ እመርታ ታይቷል ብለዋል፡፡

የበጋ መስኖ ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ያሉት አቶ አንተነህ፤ 15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል ፡፡

በምክክር መድረኩ  የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የክልሎች የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ነገ ደግሞ  በደቡብ ክልል የተከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድ መርሃ ግብሩ ያመለክታል።