ከሀዲው የህወሓት ቡድን ንፁሃንን በጅምላ በመረሸን ዓለም አቀፍ ወንጀል ፈፅሟል- ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

ደባርቅ፣ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) ከሃዲው የህወሓት ቡድን ንፁሃንን በጅምላ በመረሸን ዓለም አቀፍ ወንጀል ፈፅሟል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አስታወቁ።

የፌዴራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በአሸባሪው በድን በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖችን የቀብር ቦታ ጎብኝተዋል።

የማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው የህወሀት ቡድን ለ27 ዓመት የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በእርስ ሲያባላና እንዲጠራጠር ሲያደርግ የኖረ የክፉዎች ስብስብ ነው።

ቡድኑ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊያንን ካላጠፋሁ በማለት ንፁሃንን በጅምላ በመረሸን ዓለም አቀፍ ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።"የጭና ህዝብ ከፍተኛ መስዋትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አስቦ የመጣውን ወራሪ ሃይል ቅስም በመስበር ለመላው ኢትዮጰያዊያን ባለውለታ ሆኗል"ብለዋል"አሸባሪው ቡድን ዳግም በኢትዮጵያ ምድር መሰል ዘግናኝ ግፎችንና ጭፍጨፋዎችን እንዳይፈፅም በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ይደመሰሳል" ሲሉም ተናግረዋል።

"መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጭና ህዝብ ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ ልቡ ተሰብሯል" ያሉት ዶክተር ቢቂላ የጠፋው ንብረትም ሆነ የፈረሰው መኖሪያ ቤት በኢትዮጵያዊያን ለጋስ እጆች ዳግም ወደ ነበረበት ይመለሳል" ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ንፁሃንን በግፍ በመጨፍጨፍ እየፈፀመ ባለው ድርጊት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚጠየቅበት ጊዜም ሩቅ እንደማይሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

''ጭና ላይ ወደ ፊት ሁለት አይነት ታሪክ ይመዘገባል'' ያሉት ደግሞ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።"በጭናና አካባቢዋ ህዝብ ላይ የህወሓት አሸባሪ ቡድን የፈፀመው ዘግናኝ የአረመኔነት ታሪክና የጭና ህዝብ ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት ሲዘከር ይኖራል" ሲሉ አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የመጣውን ሃይል አሳፍሮ በመመለስ በከፈላችሁት መስዋእትነት መቼም የማይደበዝዝ አኩሪ ታሪክ መፃፍ ችላችኋል" ብለዋል።

"መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖች በኢትዮጵያዊያን ታሪክ ሲዘከሩ ይኖራሉ፤ በዚህ የችግር ወቅትም የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ከጎናችሁ ነው፤ ወደ ፊትም ከጎናችሁ አይለይም" ሲሉ አስታውቀዋል።

የስራ ሀላፊዎችና የአመራር ቡድኑ በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖችን የቀብር ቦታ፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች፣ በማይፀብሪ ግንባር እየተፋለመ የሚገኘውን የፀጥታ ሃይል የመጎብኘትና የማበረታታት ስነ ስርዓት አካሄዷል።የስራ ሀላፊዎችና የአመራር ቡድኑ በአካባቢው ሌሎች ጉብኝቶችን የቀጠለ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም