አሜሪካ በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል በመፈጸሟ ልትጠየቅ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል በመፈጸሟ ልትጠየቅ ይገባል ተባለ
መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል የፈጸመች በመሆኑ በተባባሩት መንግስታት ድርጅት ልትጠየቅ ይገባል ሲሉ ቻይና እና ኢራን ጠየቁ፡፡
አገራቱ በመደበኛ አሰራር መሰረት ደብዳቤአቸውን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን ውስጥ የጦር ወንጀሎችን ፈጽሟል ያለችው ቻይና፤ “ለፍርድ ይቅረቡ” የሚል ደብዳቤ ባሳለፈው ማክሰኞ ዕለት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቅርባለች።
ደብዳቤው ከቻይና በተጨማሪ ቦሊቪያ ፣ ቡሩንዲ ፣ ኩባ ፣ ኢራን ፣ ሰሜን ኮሪያ ፣ ሩሲያ ፣ ቬንዙዌላ በመወከል ነው የቀረበው ተብሏል።
"በአፍጋኒስታን ውስጥ በአሜሪካ የሚመራው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ የሰብአዊ ቀወስ እንዲፈጠር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል" በማለት በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡
እ.ኤ.አ ከሚያዚያ ወር 2020 ጀምሮ በጦርነቱ ቢያንስ 47 ሺህ ንፁሃን የአፍጋኒስታናዊያን ዜጎች ተገድለዋል፤ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውም ተገልጿል።
የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ወታደሮች የጦር ወንጀሎች የተፈጸመ በመሆኑ "በገለልተኛ ወገን በጥልቀት መመርመር አለበት" ሲሉ ጥያቄቸውን አቅርበዋል ።
በድብዳቤው ላይ "የጦር ወንጀል የፈጸሙ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፤ ተጎጂዎች ፍትህና መፍትሔ ይገባቸዋል ” ሲል አቋማቸውን ገልጽ አድረገዋል።
“ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ በ20 አመት ቆይታቸው የአፍጋኒስታን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በእጅጉ አደፍርሰዋል ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ጎድተዋል፣ የሰብአዊ መብት በሚጥስ መልኩ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን አድረገዋል ሲሉ ኮንነዋል፡፡
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኬኔዲ ትምህርት ቤት እና ብራውን ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀረው መረጃ መሠረት በማድረግ ፤አሶሺየትድ ፕሬስ ባወጣው መረጃ ከ 2001 እስከ ሚያዝያ 2021 ድረስ 2ሺህ 448 የአሜሪካ አገልግሎት ሰጪ አባላት ከ 3ሺህ 846 ተቋራጮች ፣ 66 ሺህ የአፍጋኒስታን ወታደራዊ እና ፖሊስ አባላት፣ 47ሺህ 245 ንጹሃን ዜጎች ፣ 1ሺህ 144 የኔቶ እና የአጋር አባላት ፣ 444 የተራድኦ ሠራተኞች እና 72 ጋዜጠኞች እንደሁም 51 ሺህ 191 የታሊባን አባላት እና ሌሎች የተቃዋሚ ቡድኖች አባላት ተገድለዋል።
የቻይና ደብዳቤ የቀረበው አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ሀገሪቱን ለቃ ከወጣች እና ከ120 ሺህ በላይ ሰዎችን ከሀገሪቱ ካወጣች በኋላ መሆኑ ነው።
ታሊባን “በአፍጋኒስታን ውስጥ ወሳኝ ወታደራዊ እና የፖለቲካ ኃይል” በማለት በሐምሌ ወር በሰላም ፣ እርቅ እና መልሶ ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የሚጠበቅ መሆኑን ቻይና መገለጿ ይታወሳል ።
በተመሳሳይ ታሊባን ለቻይና ያለውን አድናቆት ገልጾ በአፍጋኒስታን መልሶ ግንባት ሂደት እንደ “ዋና አጋር” እንደሚቆጥራት አሳውቆ ነበር፡፡
የታሊባኑ ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ “ቻይና የእኛ ዋና አጋር ትሆናለች ይህም ለእኛ ትልቅ ዕድል ነው ብሏል በወቅቱ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የቻይና እና የታሊባን ግንኙነት “አዎንታዊ ነገር” ነው ሲሉ ገልጸውታል።