የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ ተዘጋጅተናል

81

አዲስ አበባ፤ መስከረም 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሚሄዱባቸው የዓለም ክፍሎች የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርት ቤተሰብ አባላት ገለጹ። ስፖርተኞች በኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

ስፖርተኞች በኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

የስፖርቱ ማኅበረሰብ አባላት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻን የተቀላቀሉበት መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

መርሃ ግብሩን የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር፣ ምክትል ኮሚሽነሩ ዱቤ ጂሎና "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታሰደ አስጀምረውታል።

ታዋቂ አትሌቶች፣ የእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ዳኞችና የስፖርት አሰልጣኞችም ተሳትፈዋል።

ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ማስረዳትና የህወሓት ቡድን እየፈጸማቸው ያሉ እኩይ ተግባራትን ማጋለጥን ዓላማ ያደረገው "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም ነው የተጀመረው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርቱ ማኅበረሰብ አባላትም በዘመቻው የኢትዮጵያ ድምጽ በመሆን የአገራቸውን እውነት ለማስረዳት ዕድል በማግኘታቸው ደስታና ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

ከስፖርት መርሆዎች መካከል ዋነኛው ሠላም እንደሆነና ስፖርት ሠላምና ወንድማማችነትን እንደሚሰብክ ገልጸው መርሃ ግብሩ ከዚህ አንጻር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሠላምን የምትሻ፤ ከራሷ አልፎም የጎረቤቶቿና የአፍሪካን ሠላም ማስጠበቅ የምትሻ አገር መሆኗን በሚያገኟቸው መድረኮች ሁሉ ለማስረዳት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በሯሷ መፍታት የምትችል መሆኗን፤ ሊከፋፍሏት ለሚሞክሩ ሃይሎች በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ የማትደራደር እንደሆነች በምንሄድበት የዓለም ክፍል ሁሉ ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል የስፖርት ማኅበረሰብ አባላቱ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን እየፈጸማቸው ያሉ እኩይ ተግባራትን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት በሙያቸው አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የስፖርቱ ማኅበረሰብ አባላት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ ላይ በስፋት በመሳተፍ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ማሳወቅ ይገባቸዋልም ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የህወሓትን ድርጊት በማጋለጥና የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበልና እንደምትቃወም ለዓለም አቀፉ በማስረዳት የኢትዮጵያ አለኝታነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ከዘመቻው በተጨማሪ የስፖርት ቤተሰቡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቀበታልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው የስፖርት ቤተሰቡ በዘመቻው በተጠናከረ መልኩ በመሳተፍ አገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታደሰም ስፖርተኞችን ጨምሮ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻው በመሳተፍ የኢትዮጵያን እውነታ የማሳወቁ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ዩዝ ኢምፓወርመንት ማኅበርና አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም