የአሸባሪው ህወሃትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለማጋለጥ የዲጂታል ዲፕሎማሲው ሚና ከፍተኛ ነው

79

ሆሳዕና፤ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሀትን ሀገር አፍራሽ ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለዓለም ማህበረሰብ ለማጋለጥ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ሁሉም እንዲቀላቀል በጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሳ አህመድ ጠየቁ።

"እኔም ለሀገሬ ዲፕሎማት ነኝ" በሚል መሪ ሀሳብ በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዲጅታል ዲፕሎማሲው ንቁ ተሳታፊ መሆን አለበት።

አሸባሪው ህወሀት ሀገር ለማፍረስ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት አለም አቀፉን ማህበረሰብ እያሳሳተ እንደሚገኝ ጠቁመው ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ለማጋለጥ ትዊተርን በመጠቀም እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እንዳመጣም ተናግረዋል።

“በዜግነት ዲፕሎማሲው ዘርፍ አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቃል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዚህ አንጻር በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ለማምከን ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ መምህራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎቻቸውን በዲጅታል ዲፕሎማሲው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አግኝተው የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ሁሉም ዜጋ ሀገር ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሴራ ለማምከን መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በደቡብ ክልል የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የስልጠና ምርምርና ሱፐርቪዥን ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ መሉ በበኩላቸው “የሽብር ቡድኑን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሰሩ ምዕራባውያን ዕውነታውን እንዲያውቁት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውነታውን እየተረዳው የመጣ ቢሆንም፤ አሸባሪው ቡድን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር በሚያስችል መልኩ ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ብጽግናና ለውጥ የማይፈልጉ የውስጥና የውጪ ኃይሎችን ሴራ ለማምከን ዩኒቨርሲቲው በዲጂታል ዲፕሎማሲው በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲፕሎማሲ ስራው ለመንግስት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር ወደ ፊትም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዲጅታል ዲፕሎማሲውን በመቀላቀል ሀሳቡን እዲያሰማ የተጀመረው የትዊተር ዘመቻ በሌሎችም መረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ሀሳቡን የሚያስተላልፍበትና ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያጋልጥበት ሁኔታ ተመቻችቶ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በመድረኩ በደቡብ ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የፌዴራልና የክልል ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም