የዩኒቨርሲቲ – ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር የትምህርት ሥርዓቱ ያለበትን ክፍተት ይሞላል

343

ሀዋሳ፤ መስከረም 06/2014 (ኢዜአ) የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር የትምህርት ሥርዓቱን ክፍተት በመሙላት ሰልጣኞችን ለሥራው ዓለም ብቁ ለማደረግ እንደሚበጅ የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ደረጃ ዶት ኮም በጋራ ያዘጋጁት ዓመታዊ የሥራ አውደ ርዕይና የምክክር መድረክ በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን  በበይነ መረብ ለተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ስርዓቱ በተደራሽነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል።

ይሁንና ሰልጣኞች ስራ በማፈላለግና ሊያሟሉ ከሚገባቸው እውቀትና ክህሎት አንፃር ክፍተት አለበት ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለተመራቂዎች ተገቢ የክህሎት ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ከቀጣሪ ተቋማት ጋር እንዲገናኙ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ሰልጣኞችን ብቁ በማድረግ ክፍተቱን ለመሙላት ስለሚያግዝ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ኮሚሽነሩ ያመለከቱት።

ተመራቂዎች በሀገር ውስጥና ውጭ በሚገኝ የሥራ ዕድል ብቁ ሆነው እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ተቋማትና አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መሳይ ኃይሉ ፤ ዩኒቨርሲቲው የተመራቂዎችን የመቀጠር መጠን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለእዚህም ሥራውን በባለቤትነት የሚያከናውን ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው መቋቋሙን  ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ ዩኒቨርሲቲው በምሩቃን የሥራ ቅጥር ሁኔታ ላይ ያተኮረ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የቀጣሪ ተቋማትና የተማሪዎችን ፍላጎት ያማከለ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና የፕሮግራም ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

“የሥራ አውደ ርዕዩ ከ2 ሺህ በላይ ተመራቂዎች ከ35 ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በግንባር የሚገናኙበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደረጃ ዶት ኮም ፕሮግራም ዳይሬክተር ወይዘሮ ሲሀም አየለ ናቸው።

በቅጥር ወቅትና በሥራ ዓለም ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ፈተናዎችና ማሟላት ካለባቸው ክህሎት አኳያ በቂ ሥልጠና እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመሰል አውደ ርዕዮች ከሚሳተፉ ተማሪዎች መካከል በቀጣይ ስድስት ወራት ከ6 ሺህ ያላነሱ ተመራቂዎችን ስራ ለማስያዝ አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ ከተሳተፉ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ወንድማገኝ ይስሀቅ በሰጠው አስተያየት “ከዚህ በፊት ከምረቃ በኋላ ቀጣሪ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት ቀርቶ በአውደ ርዕዩ ከቀጣሪዎች ጋር ከወዲሁ መገናኘታችን ብዙ ሸክም ያቃልላል” ብሏል።

ሌላዋ ተመራቂ ተመሪ ሜላት ግርማ፤  ከዚህ በፊት ተቀጥራ እሰራበታለሁ ብላ የምታስባቸው ተቋማት ውስን እንደነበሩ ገልፃ በአውደ ርዕዩ ተጨማሪ የሥራ ዕድል የምታገኝባቸውን ቀጣሪ ድርጅቶች መተዋወቋን ገልፀለች።

በአውደ ርዕዩ ከተሳተፉ ቀጣሪ ድርጅቶች መካከል የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሻሸመኔ ዲስትሪክት የሰው ሀብት ኦፊሰር አቶ ከድር በሪሶ አንዱ ናቸው።

አውደ ርዕዩ ከዚህ በፊት ለቅጥር ይከተሉት የነበረውን ሂደት በብዙ በማሳጠር ተፈላጊውን የሰው ሀይል በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ነፃ የሆነ ተቀጣሪ ለማግኘትም ምቹ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።