"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ንቅናቄ የተሳሳተ አቋም የያዘውን የአሜሪካ መንግስት ሀሳብ እንዲለውጥ ይረዳል

93

መስከረም 6/2014 (ኢዜአ)  "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ንቅናቄ በተዛባና በተሳሳተ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መረጃ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ አቋም የያዘውን የአሜሪካ መንግስት ሀሳብ ለማስለወጥ እንደሚረዳ የተፎካካሪ ፖለተካ ፓርቲ አመራር አባላት ተናገሩ።
የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለተካ ፓርቲ አመራር አባላት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ንቅናቄን በመቀላቀል በዛሬው እለት ፊርማቸውን አኑረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዴንት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀመንበር  ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ጨምሮ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም ዘመቻውን በመቀላቀል ፊርማቸውን ያኖሩት።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላቱ የንቅናቄው ዓላማ የአገር ጉዳይ በመሆኑ "በዘመቻው በመሳተፍ ግዴታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

በተለየም በአንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የተዛባና የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህን የተሳሳተና የተዛባ መረጃ በመቀልበስ ረገድ ንቅናቄው አስተዋፆ የጎላ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ እንደቆሙ ገልጸዋል።

ወጣቶች በተሳሳተ ግንዛቤ አቋም የወሰደውን የአሜሪካ መንግስት እውነታውን ለማሳወቅ በቁርጠኝነት በመነሳታቸው እንደኮሩባቸው ተናግረዋል

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ "የእናት አገሬ ጉዳይ አሳስቦኝና እንቅስቃሴው በጣም አስፈላጊ ሆኖ ስለታየኝ ዘመቻውን ተቀላቅያለሁ" ብለዋል።

የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ባቀረቡት የተዛባ መረጃ ላይ ተመርኩዞ አቋም ያዘው የአሜሪካ መንግስት እውነታውን ተረድቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ እንደሚያደምጥ እምነታቸውን ተናግረዋል።

የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጤት እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ "ለአገራችን እኛ መስዋትነት ካልከፈለን ሌላ የሚከፍልልን ስለሌለ የተራራቀ ሀሳብ ቢኖረንም በአገር ጉዳይ አንድ ጽኑ አቋም ነው ያለን" ብለዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዚዴንት አቶ ማሙሸት አማረ፤ "በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ የተዛቡ መረጃዎችን በማጥራት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያን ለማዳን መረባረብ ግዴታው መሆኑን ነው ያሳሰቡት።

በንቅናቄው የኢትዮጵያን እውነተኛ መረጃ ለዓለም ማህበረሰብ ማድረስና ማስረዳትም ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የአሸባሪው ህወሓት "አገር የማፍረስ ሴራ እንዲሁም የጅምላ ግድያና ዘረፋ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል" ብለዋል ፓርቲዎቹ።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" መርሃ ግብር እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም