አልማ ግምታቸው 18 ሚሊዮን ብር የሆነ አጋዥ መጻህፍትና ኮምፒውተሮችን ድጋፍ አደረገ

325

ደብረማርቆስ፤መስከረም6/2014(ኢዜአ) በአልማ የምስራቅ ጎጃም ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ግምታቸው 18 ሚሊዮን ብር የሆኑ ከ44ሺህ በላይ አጋዥ መጻህፍትና ላብቶፕ ኮምፒውተሮችን ድጋፍ አደረገ።

በውጭ  ከሚኖሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን ተወላጆች  የተገኘው  ድጋፉ  በዞኑ ለሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እንደሚከፋፈል ታውቋል።

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዘላለም አንዳርጌ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፤ማህበሩ ለሰው ሃብት ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በዚህም በውጭ  የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች በትምህርት ዘርፍና ሌሎች የልማት ሥራዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስተባበሪያው መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የበኩሉን እገዛ እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ተወላጆቹን በማስተባበርም 18 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው 44ሺህ 434 አጋዥ መጻህፍት እና 6 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

በዞኑ ድጋፍ የተደረገላቸው ወረዳዎች ደብረኤሊያስ፣ እነብሴ ሳርምድር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎዛምን፣ ስናን እና ባሶሊበን ወረዳዎች ናቸው።

ማህበሩ በተጨማሪም በአሸባሪው ቡድን ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በተፈናቀሉ ወገኖች ላይ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይከሰት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ስለሺ ተመስጌን በበኩላቸው፤አልማ የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር ያደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

አዳዲስ በሚገነቡና በነባር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ይስተዋል የነበረው የአጋዥ መጻህፍት እጥረት ለማቃለል ይረዳል ነው ያሉት።

የአካባቢው ተወላጆች በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ለሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ በጎፈንድ በኩል እያሰባሰቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የደብረ ማርቆስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታደሰ አምበሉ “መጻህፍቱ ተማሪዎችን በእውቀትና ክህሎት አንጾ ለማውጣት ይረዳል” ብለዋል።

በአልማ አስተባባሪነት ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።