የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲዘገይ ያደረገው የግብጽና የሱዳን መወላወል ነው

63

መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲዘገይ ያደረገው ግብጽና ሱዳን ወደ ድርድሩ ላለመግባት ያሳዩት መወላወል ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በፐብሊክ ዲፕሎሲ በሳምንቱ የተከናወኑት አባይት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ አሁንም የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ሆኖም ግብጽና ሱዳን ድርድር ውስጥ ላለመግባት ያሳዩት መወላወል ለሂደቱ መዘግየት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን በነበረው ሂደትና በቀጣይ ጊዜያትም የሶስትዮሽ ድርድሩ መተኪያ የሌለው እንደሆነ የሚገልጹ መልዕክቶች  ጠንክረው እየመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከምክትል ጠቅላይ ሚነትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መምከራቸውንም ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንና ወደ ሱዳንና ግብጽ በመሄድ በዚሁ አግባብ የሚነጋገሩ መሆኑን መግለፃቸውንም ጠቁመዋል።

ድርድሩ በዚህ ጊዜ ይጀመራል ተብሎ ባይቀመጥም ኢትዮጵያ ለሶስትዮሽ ድርድሩ ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ በማንኛውም ሠዓት ዝግጁ ናት ብለዋል አምባሳደር ዲና።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ኢትዮጵያ ለድርድሩ የምታሳየውን የጸና አቋም አገራቸው የምታደንቀው መሆኑን መናገራቸውንም አንስተዋል።

የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍትሄ የሚለውን ሃሳብ ኮንጎ አጥብቃ የምትደግፍ መሆኑን በመግለጽ በዚሁ መንፈስ አገራቸው የሶስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ጥረት እንደምታደርግ መግለጻቸውንም ነው ያወሱት።

ቃል አቀባዩ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔን በተመለከተ ጉዳዩ የልማትና ውሃን በአግባቡ የመጠቀም ጉዳይ መሆኑን በተገነዘበ መልኩ መሆኑንም አንስተዋል።  

በጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ኢትዮጵያ ከምትጓዝበት ፍትሃዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም አቋምን በመረዳት አስተዋጽኦ ላደረጉት ሀገራት ምስጋናቸውንም ገልጸዋል።

ነገር ግን ቱኒዚያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ተገቢ ባለመሆኑ ይህን ሚና መጫወት እንዳልነበረባት ተናግረዋል።

 ከሁለት ወራት በፊት ግብጽና ሱዳን ግድቡን በሚመለከት በጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ኢትዮጵያ ምላሿን እንዳቀረበች ተገልጿል።

ምክር ቤቱም የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም