አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ መሆኑን በግብጽ ሚዲያ በይፋ አረጋግጧል

376

አዲስ አበባ፣ መስከረም 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት “የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈልጉ ጠላቶች ተላላኪ መሆኑን በግብጽ ሚዲያ በይፋ አረጋግጧል” ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለማየሁ ተናገሩ፡፡

አቶ ተስፋዬ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ የውጭ አካላት አጀንዳ አስፈጻሚ እንደነበርም ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የቡድኑ አፈ-ቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ “ቴን ቲቪ” ከተሰኘና ከግብጽ መንግስት የደህንነት መዋቅር ጋር ቁርኝት እንዳለው በሚነገርለት ሚዲያ ላይ በመቅረብ ቡድናቸው እንደአሸባሪው ሸኔ ካለ ቡድን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩና ይህም እየተሳካላቸው እንደሆነ ገልጿል።

በተለይም የጀመሩትን አገር የማፍረስ ተግባር ከዳር ለማድረስ የሚያስችላቸው ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የገለጸው።

የቡድኑ አፈቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ በግብጽ ሚዲያ በመቅረብ የአሸባሪውን ህወሃት አገር የማፍረስ እኩይ አጀንዳ መግለጹን ጠቅሰው፤ ይህም ቡድኑ ካለው መሰረታዊ ባህሪ አኳያ ብዙም የሚደንቅ አለመሆኑን አንስተዋል።

የአሸባሪው ቡድን አፈ-ቀላጤ በግብጽ ሚዲያ በመቅረብ ያስተላለፈው መልዕክት፤ “አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ መሆኑን በግብጽ ሚዲያ በይፋ ያረጋገጠ ነው” ብለዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገው ሙከራ አሳፋሪ ግን ደግሞ የማይሳካ ከንቱ ቅዠት መሆኑንም ነው ያብራሩት።

አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት “ግብጾች ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ” ሲል ክስ ሲያቀርብ እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑ በግብጽ ሚዲያ መግለጹ፤ “ምን ያህል በቅዥት ውስጥ እንዳሉ ያሳያል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ “የአሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ መቼውንም ቢሆን አይሳካም” ሲሉ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር “የመነጠል ድብቅ አጀንዳ ይዞ ሲንቀሳቀስ ነበር” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ቡድኑ በግብጽ ሚዲያ ያነሳው ሃሳብም ይህንኑ እኩይ ዓላማውን ያመላከተ መሆኑ ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ ለብቻው በመነጠል እንደፈለገ ሊፈነጭበት እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ የቡድኑን እኩይ ተግባር እንደማይቀበለው ተናግረዋል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሀገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪ ቡድኑ ቀንበር ነጻ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አቶ ተስፋዬ ጠይቀዋል።

የአሸባሪው ህወሃት አፈ-ቀላጤ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚናገረውን በግብጽ ሚዲያ በይፋ በመናገር የቡድኑን ዓላማ በግልጽ አሳውቋል።