በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የመቀላቀል እድል በማግኘታችን ኩራትና ደስታ ይሰማናል

185

መተማ ፤ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማዳን በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የመቀላቀል እድል በማግኘታችን ኩራትና ደስታ ይሰማናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ሠራዊቱን ለመቀላቀል እየተመዘገቡ ያሉ ወጣቶች ተናገሩ።

የገንዳ ውሃ ከተማ  ወጣቶች የመንግስትን ሀገር የማዳን ጥሪ በመቀበል በነቂስ ወጥተው  መመዝገብ መጀመራቸው የሚደነቅ ነው።

በላይነህ ሲሳይ በከተማዋ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ከተመዘገቡት ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።  

ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የህልውና አደጋ ለመታደግ  መከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀል አማራጭ  የሌለው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው ወጣት በላይነህ  ለኢዜአ የተናገረው።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን  መቀላቀል  የልጅነት ህልሙ እንደነበር አስታውሶ፤  ለሀገር መስራትና መስዋዕት መሆን ኩራትና ክብር ነው ብሏል።

ወጣት አበራ መንግስቴ በበኩሉ፤ ሰላም የሰፈነባትና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለማስጠበቅ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ  የሀገር መከላከያ  ሠራዊትን የመቀላቀል እድል በማግኘታችን  ኩራትና ደስታ ይሰማናል ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ  መሆኑን የተናገረው  ወጣቱ ”አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር እኔም የአባቶቼን ፈለግ በመከተል የታፈረችና የተከበረች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የድርሻዬን እወጣለሁ ብሏል።

ከውስጥም ከውጭም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎች  ጠላትን የሚያሳፍሩ ውድ ልጆች ያሏት መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ አመልክቷል።

ሀገርን በማዳን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም በአንድነት መዝመት እንደሚጠበቅ የተናገረችው ደግሞ ወጣት ብርቱካን ጋሻው ናት።

ሀገር በጠላት ተከባለች ያለችው ወጣቷ፤ ጠላትን ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካል መሆን  ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ሠራዊቱን ለመቀላቀል መወሰኗን ተናግራለች።

”ሴቶች ከወንዶች  እኩል ታሪክ ሰርተው ሀገራቸውን እንደሚጠብቁ ከእቴጌ ጣይቱ ታሪክ መማር አለብን” ያለችው ወጣቷ ፤ ሌሎች ሴቶችም ይህን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርባለች።

የገንዳ ውሃ ከተማ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስፋው ከተማ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን እና የፀጥታ አካሉን ለማጠናከር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ የወጣቱ ተሳትፎ የሚያኮራ መሆኑን ነው የገለጹት።

”አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቋም በሴራ በአንድ መንደር ሰዎች እንዲመራና እንዲደራጅ በመደረጉ ወጣቱ የሀገር ኩራትና ክብር የሆነውን ተቋም ለመቀላቀል አይደፍርም ነበር” ሲሉ አስታውሰዋል።

 የሽብር ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ በሚያደርገው ትንኮሳ ወጣቶች ሠራዊቱን በመቀላቀል ሀገር የማዳን ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አስፋው ገለጻ፤ ወጣቶቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን  ለማጠናከር እያሳዩት ያለው ተነሳሽነት የኢትዮጵያን ቀደምት ገናናነት የሚመልስ መሆኑን ነው።

የገንዳ ውሃ ከተማ ወጣቶች የመንግስትን ሀገር የማዳን ጥሪ በመቀበል በነቂስ ወጥተው  መመዝገብ መጀመራቸው የሚደነቅ ነው ያሉት  ኃላፊው፤ የሴቶች ተሳትፎ  የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ከመቀላቀል በተጨማሪ ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢውን እየጠበቀ  መሆኑን በመጥቀስም  ምስጋና አቅርበዋል።