ጃፓን በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ የስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች

67

መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) ጃፓን በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ የስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች።

የጃፓን መንግሥት ስምምነቱን ከተስፋ ፋውንዴሽን እና የሪሰረክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት  ከተሰኘ የልማት ድርጅት ጋር ነው የተፈራረመው፡፡

ድጋፉ በደቡብ ክልል ከንባታ ጠንባሮ ለሚገኘው ኮሎሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ ለሚገኘው ዩዎ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ልጆች ለአገር እድገትና ልማት ሁነኛ የወደፊት ተስፋዎች ናቸው።

መሰረታዊ ትምህርትን መስጠት ለልጆች እድገት ብቻ ሳይሆን ለአገር የወደፊት ዕጣ ፈንታም አስፈላጊና ወሳኝ ኢንቨስትመንት መሆኑንም ገልጸዋል።

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የሚያደርገው እገዛ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

የሪሰረክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ቢንያም በላቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በየአካባቢው ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ይቀራሉ።

በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ የሚገኘው ዩዎ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ450 በላይ ተጨማሪ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።   

የተስፋ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር አቶ ይነበብ ጌታቸው፤ "ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ተማሪዎች ተገቢውን የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል።

የጃፓን መንግሥት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1989 ጀምሮ ከ400 በላይ የማህበረሰብ ዓቀፍ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ መገንባት መቻሉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም