ምልምል ወታደሮች የተጣለባቸውን አደራ በቁርጠኝነት ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ምልምል ወታደሮች የተጣለባቸውን አደራ በቁርጠኝነት ሊወጡ ይገባል

መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) ምልምል ወታደሮች አገር በቅብብሎሽ እንደምትቀጥል በመገንዘብ የተጣለባቸውን አገር የመጠበቅ አደራ በቁርጠኝነት እንዲፈጽሙ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ አሳሰቡ።
የቡልቡላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መሰረታዊ ስልጠና የወሰዱ ምልምል ወታደሮችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋና ሊቀመንበሩ አቶ የሺዋስ አሰፋ ተገኝተዋል።
ወታደሮቹ የተኩስ፣ የውጊያ ስልት፣ ወታደራዊ ሰልፍና ግዳጅን በላቀ አፈጻጸም መወጣት የሚያስችላቸውን ስልጠና ተከታትለዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ኢትዮጵያ ቀድሞም ከውጭ ጠላት ጋር አብረው የሚወጓት ባንዳ አጥታ እንደማታውቅና የጁንታውም እንቅስቃሴ ከዚህ የተለየ አይደለም ብለዋል በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ።
ኢትዮጵያ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቿ የሚገጥማትን ፈተና የምትወጣው የቁርጥ ቀን ልጆቿ በሚከፍሉት መስዋዕትነት መሆኑን ገልጸው ተመራቂ ወታደሮችም የአገር ህልውና የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አገር ባቀረበችው ጥሪ መሰረት እናት፣ አባት፣ ቤተሰብ ሳትሉ ለመስዋዕትነት ራሳችሁን በማዘጋጀታችሁ ትልቅ ክብር ይገባችኋል ሲሉም አክለዋል።
"ኢትዮጵያ ጦርነቱን በእርግጠኝነት ታሸንፋለች" ሲሉም ነው ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ የተናገሩት።
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ህወሓት ኢትዮጵያ ላይ የደቀነው አደጋ ሁላችንንም የሚነካ በመሆኑ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
አገር የገባችበት ፈተና ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከዚህ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
"ለአገራችን በችግሯ መድረሳችሁን እንረሳ ዘንድ ንፉጎች አይደለንም፤ በተዋደቀላት አገር ሠራዊታችን ተገቢውን ክብር አግኝቶ እንዲኖር በሙሉ አቅማችን እንሰራለን" ሲሉም አረጋግጠዋል።
"ወድቃችሁ ስለምታቆሙን፣ ሞታችሁ ስለምታኖሩን፣ ስግብግነትና ሌብነት በነገሰበት ዘመን ራሳችሁን አሳልፋችሁ ስለምትሰጡን፣ ሆዳሞች ከድሃ ሲቆርሱ፣ በውሃ ጥም የሁላችን ደጀን ስለምትሆኑ እናመሰግናችኋለን እናከብራችኋለን" በማለት ለምልምል ወታደሮቹ ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በንግግራቸው" ምልምል ወታደሮች አገርና ሕዝባችሁን ከነፍሳችሁ አስበልጣችሁ ስለወደዳችሁ ትልቅ ስፍራ ይሰጣችኋል" ብለዋል።
የኢዜማ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም በየትኛውም አገር ልዩነትን ማስተናገድ ይቻላል በአገር ግን ልዩነት ስለሌለ ከመከላከያ ጋር በጋራ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የአዋሽ፣ ቢሾሌና ቡልቡላ ማሰልጠኛዎች አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ድሪባ መኮንን በበኩላቸው ምልምል ወታደሮች በስልጠና የቀሰሙትን ወታደራዊ እውቀት መተገበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ቡልቡላ ማሰልጠኛ ማዕከል የተገኙት ወታደሮችም የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።