ሕዝብን በማገትና በመዝረፍ ለከፋ ስቃይ መዳረግ በአፋጣኝ መቆም አለበት

መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች "ህዝብን በማገትና በመዝረፍ ለከፋ ስቃይ መዳረጉ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል" ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ።

ያለንበት ወቅት ከተረፈን ብቻ ሳይሆን ካለን ለወገኖቻችን በማካፈል እንደአገር የምንሻገርበት መሆን እንዳለበትም ነው የተናገረው።

አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴ አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፉ አድርጓል።

አትሌቱ ድጋፉን በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት በሃይሌ እና ዓለም ኢንተርናሽናል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሠራተኞች ስም ያስረከበ ሲሆን፤ ከቀያቸው ተፈናቅለው በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ወገኖችንም ጎብኝቷል።

 በክረምት ወቅት ከሞቀ ቀያቸውና ከእርሻ ስራቸው መፈናቀላቸው እጅግ እንዳሳዘነውም የገለጸው አትሌቱ፤ ያለንበት ወቅት ከተረፈን ብቻ ሳይሆን ካለን ለወገኖቻችን በማካፈል እንደአገር የምንሻገርበት መሆን እንዳለበት ተናግሯል።

በውጭም በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህን በመገንዘብ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቻቸው እንዲደርሱም ነው ጥሪ ያቀረበው።

በተጨማሪም አትሌቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

አሸባሪው ህወሃት "የትግራይና በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦችን ከመግደልና ከመዝረፍ በተጨማሪ እንዳይንቀሳቀሱ በማገት ለከፋ ስቃይ እየዳረገ ነው" ያለው አትሌት ሃይሌ፤ ድርጊቱ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ህብረት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሞከር አሳፋሪ ግን ደግሞ የማይሳካ ከንቱ ቅዠት መሆኑንም አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ተናግሯል።

ኢትዮጵያን ማፍረስ ፈጽሞ የማይቻል መሆኑንም ነው ያብራራው።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሰይፉ ሰኢድ በበኩላቸው፤ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ አካባቢዎች ተጠልለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

"አሁን ያጋጠመን ፈተና ጊዜያዊ ነው ተጋግዘን በማለፍ ልናሸንፈው ይገባል" ሲሉም ነው የተናገሩት።

የሚገጥሙን ፈተናዎች ደግሞ ወድቀን የምንቀርባቸው ሳይሆኑ አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርባቸው  መሆን እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሃይል "በምድር ላይ የሚነገሩ ግፎችን ሁሉ በህዝባችን ላይ ፈጽሟል" ያሉት የዞኑ ምክትል አስተዳደር፤ ቡድኑ "ሰላማዊ ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ ንብረት አውድሟል፤ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ገድሏል" ብለዋል።

በተጨማሪ በእርሻ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግን የሚያረጋግጠው  አሸባሪው ቡድን ሲጠፋ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አትሌት ሻለቃ ሃይሌገብረ ስላሴ በአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን በዳስ ለሚማሩ ህጻናት ያስገነባውን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤትን የአሸባሪው ህወሓት ማውደሙ ይታወቃል።

አትሌቱ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ በተፈጸመው ድርጊት እጅግ ማዘኑን በመግለጽ፤ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ማውደም በጦር ወንጀለኝነት መታየት እንዳለበትም መጠየቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም