ለኢትዮጵያ በየትኛውም አውደ ግንባር ዘማቾች ነን

329

አዲስ አበባ፣ መስከረም 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ለኢትዮጵያ በየትኛውም አውደ ግንባር ዘማቾች ነን” ሲሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች “ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በመቆም አያቶቻችን ያቆዩልንን አገር ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል፤ ለአገራችን ዘማች ወታደሮች ነን” ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተመሳሳይ አላማ ካላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጋር በማበር ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም አውደ ግንባሮች ለመዝመት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ፣ በማገዝና አብሮ በመሰለፍ ጭምር የኢትዮጵያን ጠላት መዋጋት የሁሉም ግዴታ እንደሆነም አመልክተዋል።

በቀጣይ ግንባር ድረስ በመዝመት፣ በተሰማሩበት ሙያ አገርን በትጋት በማገልገል፣ በሽብር ቡድኑ ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ በማድረስ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ስመኘው አድነው፤ የአገርን ህልውና ስጋት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግሯል።

የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል፣ በበጎ ፈቃድ ተግባራት፣ ጦር ግንባር በመሄድና በሌሎች ልዩነት ሳይገድባችው ሰፊ ተጋድሎ እያደረጉ እንደሚገኙም አመልክቷል።

በርካታ ወጣቶች የአገራቸውን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ግንባር ለተሰለፉ የጸጥታ ሃይሎች ቤተሰቦች የግብርና ስራን በማገዝ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁሟል።

የአገርን አንድነትና ክብር ለማስጠበቅ በሚደረግ ዘመቻ ወጣቱ በበጎ ፈቃድና በሌሎች ተግባራት ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልእክቱን አስተላልፏል።