በአዲስ አበባ የሚገኙ ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ 11 ትምህርት ቤቶች እውቅና ተሰረዘ

217

መስከረም 6/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ከደረጃ በታች ናቸው ያላቸውን የ11 ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፍቃድ መሰረዙን አአስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ  ሸዊት ሻንካ የትምህርት ተቋማት የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ ሂደትን አስመልክቶ  ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በመዲናዋ የሚገኙ የመንግስትም ሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ተገቢውን አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ በየሁለት ዓመቱ ምዘና እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

በመሆኑም የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የትምህርት ተቋማትን ከጥራት አንጻር የመለካት፣ ቁጥጥር የማድረግና በተቀመጠው ደረጃ መሰረት የመመዘን ስራዎች ተከናውነዋል።

የመማር ማስተማር ሂደቱን በግብዓት፣ በሰው ኃይል፣ ምቹ የመዋያና የትምህርት ስፍራና ከባቢን በመፍጠር፣ ምቹ መጸዳጃ ቤቶችና የኮቪድ መመሪያን ማሟላት ከመመዘኛ መስፈርቶቹ መካከል ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት ነባርም ሆኑ አዲስ ትምህርት ቤቶች በምዘና ሂደቱ ማለፋቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ሸዊት 75 በመቶና ከዚያ በላይ ነጥብ ያመጡ ተቋማት እውቅና ይሰጣቸዋል፤ የነባሮቹም ይታደስላቸዋል።

በዚህ መነሻነት በከተማዋ የሚገኙ 672 ነባር እና 51 አዲስ የቅድመ መደበኛ፣ የመደበኛ፣ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መመዘናቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል 723 ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው መለኪያ መሰረት 75 በመቶና ከዚያ በላይ በማምጣት የእውቅና ፍቃድና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

መለስተኛ ችግር ያለባቸውና በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራቸውን እያከናወኑ ለሚቀጥለው ዓመት ማሻሻያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው 61 ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ማሰጠንቀቂያው ከተሰጣቸው መካከል 29 የቅድመ መደበኛ፣ 28 የመጀመሪያ ደረጃና አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤያቸው እንዲሻር ለ2015 ዓ.ም የእውቅና ፈቃድ ጥያቄ አቅርበው እንዲያስፈትሹ መመሪያ እንደተቀመጠላቸውም አብራርተዋል።

ዋና ስራ አስኪያጇ ባለፈው ዓመት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው 65 ትምህርት ቤቶች 60ዎቹ በተደረገ ክትትል የደረጃ ማሻሻል በማድረጋቸው የእውቅና ፈቃድ እንደተሰጣቸው አንስተዋል።

ምንም አይነት ማስተካከያና ማሻሻያ ያላደረጉ አምስት፣ ዘንድሮ በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መስፈርቱን ያላሟሉ ስድስት ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ 11 ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሂደትም ሆነ በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የጤናና የደህንነት ስጋት የሚያሰከትሉ መሆናቸው ስለተረጋገጠ የእውቅና ፍቃዳቸው መሰረዙን አስታውቀዋል።

ፍቃዳቸው ከተሰረዘው መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ለ ሱፐር ኪድስ፣ ኢንዱራንስ አዲስ፣ ኤልሻዳይ ወረዳ 12፣ ጵሾን ወረዳ 9፣ ቪካስ እና ሮሆቦት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሀሞና እና እመሙዝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ሁንዴ ጉዲና የመጀመሪያ ደረጃ እና ማይ ፊፍ ቅድመ መደበኛ እንዲሁም  ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አዶናይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

ዋና ስራ አስክያጇ ፈቃድ ሳይኖራቸው ምዝገባ ያካሄዱ ትምህርት ቤቶች ስለመኖራቸው ለማጣራት በቅርቡ የፍተሻ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

እውቅና ሳይኖራቸው ተማሪ የመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ከተገኙ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው የተመዘገቡ ተማሪዎችን ሃላፊነት ባለስልጣኑ እንደሚወስድ አክለዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ያስመዘገቡበት ትምህርት ቤት እውቅና እንዳለው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

እውቅናቸው የተሰረዘ ትምህርት ቤቶች ዝርዝር በሚገኙበት ክፍለ ከተማ፣ ወረዳና ሕዝብ ሊያየው በሚችልባቸው አካባቢዎች እንደሚለጠፍም ነው ወዘሮ ሸዊት የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም