አመራሮቹ ግንባር ተገኝተው ያደረጉት ጉብኝት ለሰራዊቱ ብርታት ሆኗል

345

ደብረ ታቦር መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) ”የመገናኛ ብዙሀን፣ የኮሙኒኬሽንና የመከላከያ አመራሮች ግንባር ተገኝተው ያደረጉት ጉብኝት ለሰራዊት አባላት የሞራል ብርታት ሆኗል” ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ኮለኔል ጌትነት አዳነ አስታወቁ።

የመገናኛ ብዙሃን፣ የኮሙኒኬሽንና የመከላከያ አመራሮች በደቡብ ጎንደርና ሰሜን ወሎ ዞኖች ከአሸባሪ ቡድኑ ነፃ የሆኑ አካባቢዎችን ጎብኝተዋ።

ኮለኔል ጌትነት አዳነ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ህዝቡና ከፍተኛ አመራሩ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለው የሞራልና የስንቅ ድጋፍ ሰራዊቱን ለበለጠ ድል እያነሳሳው ይገኛል።

የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ሃላፊዎች በየግንባሩ በማሰማራት የአሸባሪ ቡድኑን ግፍና በደል በመመልከት የዓለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው በማድረግ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሆነ ገልፀዋል።

“ከዚህም ባለፈ በአካል ተገኝተው ስራዊቱን ማበረታታትና የተጎዱትን መጠየቅ መቻላቸው ለመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ መነሳሳትና ጉልበት ፈጥሯል” ብለዋል።

መካላከያ ሰራዊቱ በተቀናጀ አግባብ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እያደረገ ባለው ተጋድሎ የአማራሩና የህዝቡ ድጋፍ የሚያስመሰግንና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ እንደሆነ ተናግረዋል።

“በተለይ ህዝቡ ነጋሪ እንጂ አስተማሪ አያሻውም” ያሉት ዳይሬክተሩ ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ መስዋትነት እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን ጠቅሰው አሸባሪው ቡድን በተባበረ ክንድ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመሰስ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አመራሮቹ  በደብረ ዘቢጥ ግንባር የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት፣ ጉዳት የደረሰበትን የጨጨሆ መድሃኒያለም ቤተ-ክርስቲያንና ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማትና ሰዎች ጎብኝተዋል።