ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ያሳተመው መዝገበ ቃላትና የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

247

ሆሳዕና፤ መስከረም 6/2014(ኢዜአ) ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ አስር ቋንቋዎችና ባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ያሳተመው መዝገበ ቃላትና የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ  በተገኙበት ዩኒቨርሲቲው ያሳተመው መዝገበ ቃላትና የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ  የምርምር ውጤት መሆኑ ተመልክቷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ እንደገለጹት፤ ሀገር በቀል እሴቶችን ከጥፋት ለመታደግ የተለያዩ ምርምሮች  እየተከናወኑ  ይገኛሉ።

ከምርምሮቹም መካከል የሀገሪቱን ቋንቋንና ባህልን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል  ሀድይሳ፣ ከንባቲሳ፣ ሲዳምኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ኑዌርን ጨምሮ በአስር ቋንቋዎች አሳትመው ያዘጋጁት መዝገበ ቃላትና የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ እንደሚገኘበት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ቋንቋዎችና የተለያዩ ብሄረሰቦች ባህላዊ እሴት በአንድ ቋት በመሰነድ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችል መተግበሪያም መሰናዳቱን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብን መሰረት ያደረጉ ሀገራዊ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኤርጎጌ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የገጠመውን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ትግል በማገዝ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው ።

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ  ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ተቋሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ የሚነገሩ ቋንቋዎችና ባህል በቀላሉ እንዲያውቅ የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት በርካታ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሆን ለማስቻል የተከናወነው ስራ መበረታታት አለበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

እንደ ሀገር በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ኤርጎጌ፤  ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም ሀገራዊ መፍትሄ ማምጣት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አውስተዋል።

ይህም የብዝሃ ልሳንነት የእውቀት አድማስ እንዲሰፋ መሰረት እንደሚሆን ገልጸው፤ የሌላውን ባህልና ቋንቋ ማወቅ አብሮነትን ለማሳደግና ተግባቦትን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ስራዎችን በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የፌደራል፣ ክልልና ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።