በአሸባሪው ሀይል ለወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

77

ባህር ዳር መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) ትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ለወደሙ ትምህርት ቤቶች ለመልሶ ግንባታና ጥገና የሚውል 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ዛሬ  በባህር ዳር ከተማ  ተገኝተው ድጋፉን ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው የክልሉ አካባቢዎች የወደሙና የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና በመጠገን መልሶ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስቀጠል መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ለመጠገን ለጊዜው የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ከክልሉ ተጠራርጎ ሲወጣ በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት በዝርዝር በማጥናት ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ ወረራ በፈፀመባቸው የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በጦር ካምፕነት በመጠቀሙ እንዲወድሙ አድርጓል።

"በአሸባሪ ቡድኑ 3 ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል " ብለዋል

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያደረገው ድጋፍ አሁን ወራሪው ሃይል ተደምስሶ በወጣባቸው አካበቢዎች የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶና ጠግኖ ትምህርት ለማስጀመር አጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም