የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ተዘጋጅተናል...የአዋሽ ቢሾላ ተመራቂ ወታደሮች

182

አርሲ መስክረም 6/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለመድፈር የሚታትረውን ማንኛውንም ሃይል ለማምከን ተዘጋጅተናል ሲሉ በአዋሽ ቢሾላ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ያጠናቀቁ ተመራቂ ወታደሮች አስታወቁ ።

የአዋሽ ቢሾላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማእከል በመሰረታዊ ውትድርና ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት ዛሬ አስመርቋል።
ተመራቂ ወታደር ዮሐንስ ተገኔ ለኢዜአ እንደገለፀው  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳርድንበር ለመድፈር የሚታትረውን ማንኛውንም ሃይል ለማምከን ዝግጁ ነው።

"የእናት ጡት ነካሹ አሸባሪው የህወሀት ቡድን የምወዳት ሀገሬን በመድፈሩ ህልውናዋን ለመታደግ ወደ መከላከያ ሰራዊት ተቀላቅያለሁ" ብሏል።
በስልጠና ቆይታው መሰረታዊ  የውትድርና እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ሞራላዊ ብቃት ማግኘቱን አስታውቋል ።

"በስልጠናው አሸባሪ ቡድኑን ለመቅበር የሚያስችለኝን ብቃት አግኝቻለሁ " ሲል ገልጿል።

ተመራቂ ወታደር አባይነህ ቶለሳ በበኩሉ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጥምረት በመፍጠር ሀገሪቱን ለማፍረስና ህልውናዋን ለማጥፋት እየተፍጨረጨሩ መሆኑን ተናግራል።

የአሸባሪዎቹን ዓላማቸውን ከንቱ ለማስቀረት የሚወደውን ትምህርት አቋርጦ ወደ መከላከያ መቀላቀሉን ገልጿል።
"ሀገር እየተደፈረችና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባት እኔ የምማረው ትምሀርት የለም" ያለው ተመራቂ  ወታደር ገዛኸኝ ከ11ኛ ክፍል ትምህቱን አቋርጦ ወደ መከላከያ መቀላቀሉን ተናግሯል።
የተመራቂ ወታደር አባይነህ ወንድም ተመራቂ ወታደር መስፍን ቶለሳም  ወያኔና ሸኔ ሀገር እያመሱ መማርም ሆነ በሰላም መኖር ስለማይቻል ወደ መከላከያ መቀላቀሉን ገልጻል። 
በስልጠና ቆይታው ያገኘውን ክህሎት ተጠቅሞ ጠላትን ለማስወገድ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ ከባሌ ሮቤ አዋሽ ቢሾለ የተገኙት ወላጅ እናት ወይዘሮ ታደለች ተሰማ በበኩላቸው አንድ ብቸኛ ልጃቸው የሆነውን ወታደር ዮሀንስን ለማስመረቅ መምጣታቸውን ተናግረዋል ።

"ከሀገር በላይ ምንም ስለሌለ  የሀገሬን ህልውና ለመታደግ ልጄን ሰጥቻለሁ" ብለዋል።

ያላቸው አንድ ልጅ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት እናት  ወይዘሮ ታደለች ልጃቸው ከርሳቸው ጋር መኖር የሚችለው ሀገር ስትኖር በመሆኑ የእናት ጡት ነካሽ አውሬ እንዲወገድ ወጣቶች መከላከያን በመቀላቀል ሀገራቸውን መታደግ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ከምስራቅ ባሌ ዞን ሁለት ልጆቻቸውን ለማስመረቅ የመጡት ሳጂን ቶለሳ ቆሪቾ  በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያስተላለፉትን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ሁለት ልጆቻቸውን ወደ መከላከያ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
"ልጆቼ የተሰጣቸውን ስልጠና ተጠቅመው ሀገርን እየበጠበጡ ያሉትን ሸኔና ህወሃትን በማስወገድ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እንደሚከቱ ሙሉ ተስፋ አለኝ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም