ጤና ሚኒስቴር የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረገ

125

መስከረም 5/2014 (ኢዜአ) ጤና ሚኒስቴር የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት ፍኖተ ካርታ ይፋ አደርጓል።

የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን “ዲጂታል ጤና ሁሉን አቀፍ ለሆነ የጤና ሽፋን መሳካት” በሚል መሪ ሃሳብ የዲጂታል ጤና ኮንፍረንስ እያካሔደ ይገኛል።

የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓቱ የሚመራበት የዲጂታል የጤና ፍኖተ ካርታ እና መመሪያም የህክምና አገልግሎቱን ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ እንደሚረዳም ተገልጿል።

የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ከማሳለጡም በላይ የታካሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ የጤናውን ዘርፍ በማሳደግ ፍትሃዊነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የጤና ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎችን በመለየት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው፤ የጤና ስርዓቱን ወደ ዲጂታል ማሸጋገሩ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይም ሊከሰቱ የሚችሉ ወረሸኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ የጤና ዘርፉ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመሆኑ ስርዓቱ ገቢራዊ ሲደረግ የሳይበር ደሕንነት ስጋትን ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ መተግበር ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና መረጃ ስርዓቱ እንዲሻሻል በማድረግ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ደረጃ የሚያሻሽል መሆኑንም አስረድተዋል።

የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓቱን በአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድርግ መስራትም ይገባል ብለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው አገር አቀፍ የዲጂታል ጤና ኮንፍረንስና ኢግዚቢሽን በነገው እለት የሚጠናቀቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም