በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደው ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ

መስከረም 5 /2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻቸው ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸው በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚካሄደውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ያተኮረ ነበር።

በወቅቱም አቶ ደመቀ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት ላይ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ለተጫወተችው አዎንታዊ የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ያላትን ቁርጠኝት ገልጸው፤ይህም በሁሉም አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩልም በማንኛውም ጊዜ በድርድሩ ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡

አያይዘውም ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሰፍን በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ጽኑ ፍላጎት ጠቅሰው፤ ናይል የተፋሰሱ አገራት የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን እንደማይገባውም አንስተዋል፡፡

ክርስቶፌ ሉቱንዱላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተሳካ አገራዊ ምርጫ በማካሄዷ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ቀጥለውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ላሳየችው ቁርጠኝት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህን አጥብቃ የምታምን መሆኑና የጠቀሱት ክርስቶፌ ሉቱንዱላ ፤ የህዳሴ ግድብ ድርድርም በዚሁ መርህ መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሶስትዮሸ ድርድሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር የሚቻል ስለመሆኑም አንተስዋል፡፡

አቶ ደመቀ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ በመድረስ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን አውስተው፤ በቀጣይም ሂደቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስቀጠል የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መፍትሔ ላይ መድረስ አንደሚቻል ኢትዮጵያ በፅኑዕ ታምናለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም