የለካቲት 11ዱ እና የወይ ፍንክች ኮፍያ አጥላቂው ግለሰብ (ገሬ) ሴራ

355

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ብሎ የሽብር ቡድኑ በጦር ግንባር እየሞቱ ያሉ ወታደሮቹን አስክሬን በመጫን እየወሰደ መሆኑን እና በቀጣይ ለሚሰራቸው ድራማዎች መጠቀሚያ ሊያደርገው እንዳቀደ ጠቅሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህንኑ የመንግስት መረጃ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ዘገባ ሲ ኤን ኤን በማንኛውም ብዙሃን መገናኛዎች ሽፋን ያልተሰጠው “በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የትግራይ ተወላጆች አስክሬን ቀደም ሲል በተከዜ አሁን ደግሞ በሁመራ ወንዝ ዳርቻ ተጥለው በምርመራ አገኘሁ” የሚል የሀሰት ዘገባ አቀረበ፡፡

የመንግስትን የቀደመ መረጃ ትክክለኛነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት መሞገት የሚቻል ቢሆንም መረጃው ለሲ ኤን ኤን ብቻ እንዲሰጥ ለምን ተፈለገ? ማንስ ሰጠ? በምርመራው ላይ እነማን በእማኝነት ቀረቡ? በእነማን እንደተገደሉ የሚሳይ መረጃ ምን አለ? እና መሰል ወንጀሎችን በመፈጸም የቀደመ ልምድ እና ተሞክሮ ያለውስ ማነው? የሚሉትን አንስቶ ግልጽ ማብራሪያ መሻት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡፡

በዘገባው ላይ በመረጃ ሰጪነት፣ በማብራሪያ አቅራቢነት፣ ግርፋቱን እና ግድያውን በተመለከተ በእማኝነት እና አካባቢውን ከፊት ሆኖ በመጠቆም ጭምር ሲሳተፉ የሚታዩት የአካባቢው ተወላጆች መሆናቸው ዘገባውን ተዓማኒ አያደርገውም፡፡

ሆኖም በዚህ ድራማ ላይ በዋና ተዋናይነት የተሳተፈው ግለሰብ የህወሓት ሽብር ቡድኑ አባል እና የዚህ ድራማ አቀናባሪ ብሎም አስተባባሪ የሆነው ገሬ የተባለ ግለሰብ ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ አባል መሆኑንም በቃለ-መጠይቁ ላይ ሲቀርብ ያጠለቀው ባርኔጣ “ለካቲት 11 እና ወይ ፍንክች” የሚል ጽሁፍ ከፊት እና ከኋላ ተጽፎበት ይታያል፡፡

የዚህ ዘገባ ደራሲ እና ተዋናይ የሆነው ገሬ “በሱዳን ባህር ዳርቻ የትግራይ ተወላጆች ተገድለው ተጥለዋል” የሚል መረጃ ለጥቅም ተጋሪዋ ለሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ኒማ ኤልባጊር ሲሰጥ እና ስለግርፋቱ፣ ስለአገዳደሉ አጠቃላይ ስለሁኔታው ሲያብራራ እንዲሁም ሲመዘግብ ይታያል፡፡

ገሬ የተባለው የአሸባሪ ቡድን አባል መረጃውን ከየት አገኘው የሚል ጥያቄ መጠየቅ ብሎም የሰውየውን ተሳትፎ መጠርጠር ይቻላል።

የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ የምርመራ ዘገባ ያሉትን ለማቅረብ ሲንደረደር “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተጠያቂ ያልሆኑበትን ድብቅ ወንጀል ነው” በማለት ዘገባ እንደሰሩ አስታውሷል፤ ይህ በምን ተረጋገጠ? ሚዲያውንም በሀሰት እና ባልተረጋገጠ እንዲሁም መረጃ ባልቀረበበት ዘገባ ላይ ተመርኩዞ የቀረበ ዘገባ በመሆኑ በስም ማጥፋት ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ነው፡፡

ጋዜጠኛዋ ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ እና በጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ባሉ የኢትዮጵያ ሰራዊት ደጋፊዎች የተፈጸመ ስለመሆኑም ታነሳለች፡፡

ጋዜጠኛዋ ይህን እንድትል በገሬ እና በድራማው ተዋናዮች ተነግሯት እንጂ የተገኙት አስክሬኖች በማን እንደተገደሉ የሚያሳይ አንዳችም ፍንጭ አይሰጥም፡፡

ሚዲያው እና ጋዜጠኛዋ ይህን ድራማ ለማዘጋጀት ሲያቅዱ በዕቅዳቸው ውስጥ ያላካተቱት አንድ ትልቅ ነገር የመሰል ወንጀል አፈጻጸም ታሪክ እና ልምድን የተመለከተውን ክፍል ነው።

የዚህ መሰል ወንጀል ታሪክ እና ልምድ ባለቤት ማን እንደሆነም ጭምር ዘንግተውታል፡፡ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ እና የአገዳደል ሁኔታ ታሪካዊ ዳራን ማየት ቢችሉ ሚዲያው በዚህ ድራማ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይሆንም ነበር፡፡

ሚዲያው የሽብር ቡድኑ ደጋፊ እና ተከፋይ በመሆኑ ብቻ በሽብር ቡድኑ የተዘጋጀውን ስክሪፕት በማንበብ ተውኖታል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ማራዘሚያ ስልትነት ሲጠቀምባቸው ከነበሩ ዘዴዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ዜጎችን የማሰቃየት እና የመግደል ተግባራት ተጠቃሽ እንደነበሩ ጋዜጠኛዋ ቀደም ያሉ የሽብር ቡድኑን ባህሪያት ለማጣራት ጥረት ብታደርግ፤ አሁን በዚህ ድራማ ላይ አትሳተፍም ነበር፡፡

እንዲህ አይነት ሰይጣናዊ ስራ የቡድኑ የስልጣን መገለጫ ባህሪው መሆኑን ቀደም ሲል ከሰራቸው መሰል ወንጀሎች በመሰል የአገዳደል እና የማሰቃየት ብቃቱ በበርካታ የጉዳቱ ሰለባዎች የተመሰከረለት ስለመሆኑ ቀደም ብሎ የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች ምስክር ናቸው፡፡ ይህን የሴራ ዘገባ ነው እንግዲህ ቴድሮስ አድሃኖም “ሰይጣን ኢቭል” ሲል የጠራው፡፡

 በእርግጥ እንዲህ አይነት ተግባራት በሙሉ የሰይጣናዊ አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ መሰል ሰይጣናዊ ተግባራት ሲፈጸሙ የቆዩት ደግሞ ቴድሮስ አድሃኖም አባል እና አመራር በሆነበት በህወሃት የሽር ቡድን መሆኑ በኢትዮጵያ በስርዓቱ የተጎዱ ሰዎች የህይወት ታሪክ ማሳያዎች ናቸው።

ታዲያ አሁን ቴድሮስ ሰይጣን ሲል የጠራው የራሱን የሽብር ቡድን ወይስ ማንን? ሚዲያውም የሽብር ቡድኑ ተከፋይ ባይሆን ኖሮ በአፋር እና በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ መሰል ወንጀሎችን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ለምን ፈለገ?