አገልግሎት የማይሰጡ ወረቀቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል ተቋማት እንዲለግሱ ተጠየቀ

214

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2013 (ኢዜአ) አገልግሎት የማይሰጡ ወረቀቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል ተቋማት እንዲለግሱ የአዲስ አበባ ከተማ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ጠየቀ።

በበጀት ዓመቱ አገልግሎት ላይ የዋሉ ወረቀቶችን፣ ፕላስቲኮችንና ቁርጥራጭ ብረቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በዘርፉ ሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሰራተኞች 141 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝተዋል።

ኤጀንሲው በአዲሱ በጀት ዓመት አገልግሎት የማይሰጡ ወረቀቶችንና ካርቶኖችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከ27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኝት አቅዷል።

ኤጀንሲው አገልግሎት የማይሰጡ ወረቀቶችና ካርቶኖችን በመሰብሰብ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በተሰሩ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሐይማኖት ዘለቀ፤ ኤጀንሲው ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም የገቢ ምንጭ ለማድረግ እንዲቻልና ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጠር እየሰራ ነው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ ወረቀትና ካርቶኖችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ከተጀመረ አንስቶ በዘርፉ ለ1ሺ 200 ወጣቶች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ ተናግረዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ከተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀው፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑም እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት “አገልግሎት የማይሰጡ ወረቀቶች ምስጢራዊ ናቸው” በሚል እንደሚያቃጥሉ አመልክተዋል።

ነገር ግን ተቋሟት ወረቀቶችን ከማቃጠል ይልቅ በተደራጀ መልኩ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ለሥራአጥ ወጣቶች ሥራ በመስራት የገቢ ምንጭ ለማድረግ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ከዚህ ባለፈም ቆሻሻን ማቃጠል አካባቢን በመበከል ጭምር የጤና እክል ስለሚፈጥር ተቋማት የማያገለግሉ ወረቀቶችና ካርቶኖችን በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

በመዲናዋ በቀን ከሚሰበሰበው 3 ሺህ ቶን ቆሻሻ ውስጥ 6 በመቶውን ብቻ መልሶ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወረቀቶችን፣ ፕላስቲኮችንና ቁርጥራጭ ብረቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በዘርፉ የተሰማሩ ሠራተኞች 141 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘታቸውንም ወይዘሮ ሐይማኖት አብራርተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የቴክኖሰርቪ ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ተወካይ አቶ መስፍን ገብረፃዲቅ፤ ቆሻሻን በመሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድግ አኳያ ለኢንዱስትሪዎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደስራ በማስገባት፣ የቆሻሻ ማከማቻ ቦታዎችን በማመቻቸትና የመሰብሰቢያ ኮንቴነሮችን በማቅረብ ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡