ለኢትዮጵያ ባንኮች አፍሪ ኤግዚም ባንክ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጣቸው ነው

130

አዲስ አበባ፤ መስከረም 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር ለማቅረብ ማጽደቁን ይፋ አደረገ።

የአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለአህገራዊ ንግድ ትስስርና ልማት የማጎልበት ዓላማ በማንገብ በአውሪፓዊያኑ 1993 በግብጽ - ካይሮ የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም ነው።

ኢትዮጵያ መስራችና ባለድርሻ የሆነችበት አፍሪካ ኤገዚም ባንክ 51 የአፍሪካ አገራት በአባልነት አቅፏል።

የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ረኔ አዋምበንግ እንዳሉት፤ ባንኩ ከሌሎች አፍሪካዊ ባንኮች ጋር መወዳደር ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፍ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ይሰራል።

እስካሁንም ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ በአፍሪካ ንግድ ፋይናንስ ዘርፍ ለፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት በአፍሪካ መንግስታት ፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ገልፀው፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም ከሦስት  ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማቅረቡን ተናግረዋል።

አሁንም ተጨማሪ ለጸረ ኮቪድ ክትባት ግዥ የሚውል ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማቅረብ ከአፍሪካ ህብረትና ከሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ ሆነው በፈጣን ለውጥ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ110 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ምቹ ገበያ እንደሆነች ገለጸው፤ ባንኩ በፓን አፍሪካ ማዕቀፍ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ የንግድ ልውውጥ እንዲሰጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ባንኩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተመታው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማገገሚያም ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለባንኮች ድጋፍ መስጠቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው መድረክ ዓላማም ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ስለመሆኑ አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አጀንዳዎች ማስፈጸም በሚያስችሉ ዘርፎች ለመደገፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ባንኮች 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ባንኩ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

ባንኩ ካሁን በፊት በኢትዮጵየ በአጠቃላይ በተለያዩ ዘርፎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በመስከረም መጨረሻም ሁሉም ሂደቶች ከባንኮች ጋር ከተፈጸሙ በኋላ ብድሩ እንደሚቀርብም ግምታቸውንም ገልጸዋል፤ ለእያንዳንዱ ባንክ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቀርብላችውም አሳውቀናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፤ ባንኩ በአፍሪካ አገራት መካከልና አፍሪካን ከዓለም ጋር ያላትን ንግድ ለማሳለጥና በንግድ የማስተሳሰር ዓላማ ይዞ መቋቋሙን ተናግረዋል።

ከአፍሪ ኤግዚም ባንክ በርካታ የአፍሪካ አገራት ብድሮችና ሌሎች አገልግሎቶችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ መስራች በሆነችበት ኤግዚም ባንክ እስካሁን ተጠቃሚ እንዳልነበረች ገልጸዋል።

አፍሪ ኤግዚም ባንክ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትስስር ስኬት አንዱ አሳላጭ ተቋም መሆነን ገልፀው፤ እንደሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ እንዲከፍትም ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአፍሪካ የገቢና ወጪ (ኢምፖርት ኤክስፖርት) ባንክ ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ከባንኩ ጋር ተጠቃሚ ያለሆነችው የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች መበደር እንዳይችሉ የሕግ ከለላ ስለነበር መሆኑን አንሰተዋል።

ከሕግ ማዕቀፍ ባሻገር የኢትዮጵየ ባንኮች ከአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት በጋራ ለመስራት ልምድ ደካማ እንደነበር ገልጸው፤ በቀጣይ ግን "ይህን እድል ለመጠቀም እንሰራለን" ነው ያሉት።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እንዲሳለጥ ከሚያደርጉት አካላት አንዱ አፍሪ ኤግዚም ባንክ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ግን ባንኩ የሚሰጣቸውን አገልግሎት ኢትዮጵያ መጠቀም እንደምትሻ በመግለጽ፤ ለባንኮች የሚሰጠው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብድርም በተመለከተም ከባንኮች ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ገር መስራታቸው በተለይ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በመሆኑም የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የብድር አቅርቢነት ውሳኔ ከዚፍ አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ሌሎች የውጭ ባንኮችም በቅረበት እንዲሰሩ እንደሚበረታቱ ተናግረዋል።

የባንኩ የስራ ሃላፊዎችና የኢትዮጵያ ባንኮች አመራር አባላት ከዛሬ ጀምሮ የሦስት ቀናት የስልጠናና ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄዱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም