ከመቱ አዲስ አበባ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ ላይ የመሬት መንሸራተት በማጋጠሙ ለእንቅስቃሴ ስጋት ፈጥሯል

85

መቱ፤ መስከረም 5/2014(ኢዜአ) ከመቱ አዲስ አበባ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ ላይ የመሬት መንሸራተት በማጋጠሙ ለእንቅስቃሴ ስጋት እንደፈጠረባቸው አሽከርካሪዎችና ነዋሪዎች አመለከቱ።
በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የጅማ ዲስትሪክት በበኩሉ፤ በመንገዱ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት  የጥገና ሥራው መጀመሩን ገልጿል፡፡

የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪው አራፋት ፈቀደ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንገዱ በየዕለቱ እየተናደ በመስመጥ ላይ ስለሚገኝ ተሳፋሪዎችን ጭነው ለመጓዝ ስጋት ፈጥሮባቸዋል።

ችግሩ ቶሎ ካልተፈታ ለአደጋ ከማጋለጡም ባሻገር የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሊቋረጥ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተማሪ ጠና በለጠ በበኩሉ፤  መንገዱ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በግልጽ እየታየ አሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎችን ለመጫን እንደማያመነቱና ከጫኑም ከመደበኛው ታሪፍ በላይ እንደሚያስከፍሏቸው ተናግሯል፡፡
የሚመለከተው አካል በመንገዱ ላይ ያጋጠመውን ችግር  ትኩረት ሰጥቶ  አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥም አመልክቷል፡፡
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ጋሻሁን ዮሐንስ፤  በመንገዱ ላይ ያጋጠመው የመሬት መንሸራረት በተለይ ከባድ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው ሲያልፉ ያለው ንቅናቄ እንደሚያስፈራ ተናግረዋል፡፡
መንገዱ የኢሉባቦር ዞንና  የጋምቤላ ክልልን ከአዲስ አበባ የሚያገናኝ ብቸኛ እንደመሆኑ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የጅማ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ደነቀ ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ በመንገዱ ላይ  የመሬት መንሸራተት በማጋጠሙ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የጥገና ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት የጥገና ሥራውን ጨምሮ ቀድሞ የነበረውን የመንገዱን ግንባታ ሥራ ለማስጨረስ ከተቋራጮች ጋር ስምምነቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም