የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በመጠራቴ እድለኛ ነኝ

187

አዲስ አበባ መስከረም 05/2014(ኢዜአ) “የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በመጠራቴ እድለኛ ነኝ”

ሲል የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች ገለፁ፡፡

በጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማስልጠኛ ትምህርት ቤት በመሠረታዊ ውትድርና በ2ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት አስመርቋል።

በስፍራው በመገኘት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ ወታደሮች “በየትኛውም ግዳጅ በመሰለፍ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ወታደር አስናቀ አክሊል፤ የኢትዮጵያን ህልውና የማዳን ጥሪ ተቀብዬ ለመዝመት ስልጠናውን በማጠናቀቄ ደስተኛ ነኝ ብሏል።

በቆይታችን በቂ ስልጠና አግኝተናል፤ ለማንኛውም ግዳጅ ብቁና ዝግጁ ሆነናል ሲልም ተናግሯል።

ተመራቂ ወታደር ቸርነት መኮንን እና ምትኩ ታዬ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመሰለፍ ብቃትም፣ ወታደራዊ ጥበብም ሰንቀናል ብለዋል።

ከትምህርት ቤቱ ከአሰልጠኞች መካከል ሻምባል ማስረሻ ሀብተወልድ፤ መሰረታዊ ወታዳሮቹ በከፍተኛ ሞራል ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

በቆይታቸው በወታደራዊ ሳይንስና በተኩስ፣ በአካል ብቃትና ሌሎችም የመሰረታዊ ውትድርና ስልጠና አግኝተዋል ብለዋል።

የመከላከያ ኅብረት የሰው ኃብት ዋና መመሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሀጫሉ ሸለማ፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ውጊያ በከፈተበት ወቅት አገራዊ ጥሪን ተቀብላችሁ በእልህና ፍጹም ጀግንነት ለመሰለፍ በመዘጋጀታችሁ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።

ጀግናው የአገር መከላካያ ሰራዊት ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን በፍጹም ጀግንነት አሸባሪውን ህወሃት በመደምሰስ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመሰባሰብ ኢትዮጵያን በውትድርና ለማገልገል የተመረቃችሁ ወታደሮችም በታሪክ አጋጣሚ እድለኞች ናችሁ፤ እንኳንም ደስ ያላችሁ ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት የሃይማኖት ተቋማትን በማፍረስ፣ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንጹሃንን በመግደል ጸረ ህዝብ መሆኑን በተግባር በማረጋገጡ እስከ መጨረሻው ሊጠፋ ይገባል ነው ያሉት።

የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሎ፤ ሰልጣኞች በቆይታቸው በቂ ወታደራዊ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ በየትኛውም ግዳጅ ሰራዊቱን በመቀላቀል አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የተዘጋጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከተመራቂዎች መካከል የመሰረታዊ ውትድርናን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አየር ሃይልና፣ የኢንጅነሪንግ የሙያ ስልጠና የሚገቡ እንዳሉም ታውቃል።