በኢትዮጵያ ላይ የተያዘውን የተዛባ አመለካከት ለማረም ዘመቻው የጎላ ሚና ይኖረዋል

232

ሠመራ፤መስከረም 05/2014(ኢዜአ)በኢትዮጵያ ላይ የተያዘውን የተዛባ አመለካከት ለማረምና ትክክለኛውን ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ለማስገንዘብ "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" ዘመቻ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተመለከተ።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" ዘመቻ ዛሬ በአፋር ክልል  ሠመራ ከተማ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት፤ የብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደን እንደተናገሩት፤ የህወሃት ሽብር ቡድን እንደ መንግስት በሀገሪቱ ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ተነግሮ የማያልቅ የሰብአዊ ጥሰት፣ ኢ-ፍትሃዊ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ የበላይነት ይዞ ኢትዮጵያን መዝብሯል።

የግፍ ተግባሩ ያንገፈገፋቸው ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ቡድኑ ከስልጣን  ከወረደ  ወዲህ ሁሉንም ዜጎች በፍትሃዊነት የሚወክልና ተጠቃሚነታቸውንም የሚያረጋግጥ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ አልዋጥነት ያለው የህወሃት ሽብር ቡድን "እኔ ካልመራኋት ሀገሪቱን አፈርሳታለሁ" በሚል ትምክህት ታውሮ ሀገሪቱን ለመበተን ግልጽ ጦርነት ከፍቶብናል ብለዋል።

በጦርነቱም በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ግልጽ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በአፋር ክልል ጋሊኮማ፣  በአማራ ክልል ጭናና ማይካድራ እንዲሁም በየደረሰበት አካባቢዎች መፈጸሙን አውስተዋል።

ዘረፋና መሰረተ ልማቶችንም ማውደሙን ጠቅሰው፤ አሸባሪው ቡድን በተከፋይ አክቲቪስቶቹ አማካኝነት በሚነዛው  የውሸት ፕሮፓጋንዳ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ  ለማወናበድ መጣሩን አስረድተዋል።

ሆኖም በቅርቡ የኢትዮጵያ ወዳጆች የአሸባሪውን ቡድን  እውነተኛ ማንነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በተደረገው ጥረት  አበረታች ለውጥ ታይቷል ነው ያሉት።

የተጀመረው "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" ዘመቻ በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው የተዛባ አመለካከትን ለማረምና ትክክለኛውን ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ለማስገንዘብ የጎላ ሚና እንደሚኖረው የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አመልክተዋል።

በተጀመረው ዘመቻ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ በሰጡት አስተያየት፤ "አሸባሪው ህወሃት  በሀገራችን ላይ የከፈተብንን  ግልጽ ጦርነት በተባባረ ክንድ እየተመከተ ነው" ብልዋል።

ቡድኑ የጥፋት ድርጊቱን ለመሸፋፈን የሀሰት ወሬ በመንዛት አለምን ለማደናገር  የሚያደርገውን ሙከራ ለማክሸፍ  የማህበራዊ የትስሰር ገፆችን በመጠቀም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዘመቻም የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ወጣት አብዱቃድር መሐመድ፤ የኢትዮጵያን  እውነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ በዘመቻው ተሳትፎ ማድረጉን ተናግሯል።  

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ ያለው ሀገር የማፍረስ ሴራ የአለም ማህበረሰብ ተገንዝቦ እውነታውን ለማሳወቅ በአፋር ክልል የተጀመረው የ"ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" ዘመቻ ላይ እስከ 70ሺህ ሰዎችን ለማሳተፍ ታቅዷል።

ዘመቻው ዛሬ በሠመራ ከተማ ሲጀመር  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣  ወጣቶችና ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም