ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዲያስፖራው ከ1 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል

268

አዲስ አበባ መስከረም 05 ቀን 2014 (ኢዜአ)ባለፉት አስር አመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዲያስፖራው 1 ቢሊዮን 263 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

የዓለማችን ረጂሙ ወንዝ ዓባይ መነሻውን ኢትዮጵያ በማድረግ 6 ሺህ 671 ኪሎ ሜትር በመጓዝ በዓለም ቀዳሚው ወንዝ ነው፡፡

በወቅቱ የዓለማችን የውኃ ጂኦ ፖለቲካል ዋነኛ አጀንዳ የሆነው ከኢትዮጵያ የሚነሳው ዓባይ፤ ጥቁር አባይና ነጭ አባይ ተቀላቅለው ለሚወርዱበት ናይል 86 በመቶ የውኃ መጠን ያበረክታል።
ከዓባይ 76 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዓመታዊ ውኃ ለጎረቤት አገራት ለምትለግሰው ኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫም መሆኑ ይታወቃል።

ለዘመናት የባዕዳንን ምድር ሲያጠጣ የኖረው ዓባይ ለአብራኩ ክፋዮች ግን ከዘፈን የዘለለ የጎላ ሲሳይ አልነበረውም፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን ዓባይን በራሳቸው ሃብት እና እውቀት ለሀገራቸው ልማት፤ ለጎረቤቶቻቸው ትሩፋት ለማድረግ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመሩ አስር አመት ሞልቷቸዋል፡፡

በዚህም ባለፉት አስር አመታት ማለትም እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ 15 ቢሊዮን 931 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ አዋጥተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 14 ቢሊዮን 258 ሚሊዮን ከቦንድ ግዥና ልገሳ፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች 409 ሚሊዮን ብር ሲሰበሰብ ዲያስፖራው በበኩሉ በግንባታው ላይ የራሱን ከፍተኛ አሻራ አሳርፏል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በከፍተኛ ቁጭትና ፍላጎት በመነሳሳት ባለፉት አስር አመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን 263 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰዋል።

የዜጎች ተሳትፎ ልቆ በቀጠለበት ሂደት ከሐምሌ 1 እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ብቻ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ አገር በቦንድ ሽያጭ እና በስጦታ 201 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ 47 ሚሊዮን ብር፣ ከውጭ አገር ቦንድ ሽያጭና ስጦታ 122 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል፡፡

በአንጻሩ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የስጦታ አካውንት 447 ሺህ ብር እንዲሁም ከ8100 የሞባይል አጭር የፅሁፍ መልእክት 32 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ያደረሰን መረጃ ያሳያል።

በነሃሴ ወር ደግሞ ከ96 ሚሊዮን ብር በላይ ከሀገር ውስጥ እና ከዲያስፖራ ማህበረሰብ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች ገቢ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

ከገንዘቡ ድጋፍ በተጨማሪ መላው ኢትዮጵያዊ ለግድቡ አምባሳደር ሆነው ያከናወኗቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፎች የተጠነሰሰውን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አሻጥሮች ለመበጣጠስ ትልቅ አቅም እንደፈጠሩ ይታወቃል፡፡

በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫት እንደሚጀምሩ መገለጹ ይታወሳል።

ተርባይኖቹ እያንዳንዳቸው 350 ዋጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ በድምሩ በቅድመ ኃይል ማመንጨት ሥራው 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ ማለት ነው።

በ1960 ግንባታው ተጀምሮ በ1971 የተጠናቀቀው፤ በናይል ወንዝ ላይ የተገነባው የአስዋን ግድብ ለግብፅ የመስኖና የቱሪዝም ሃብት ከመሆኑ መተጨማሪ 2 ሺህ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክተሪክ ሃይል በማመንጨት አገልግሎት ይሰጣል።

ከዓለማችን ሰውሰራሽ ሃይቆች መካከል በግንባር ቀደምትነቱ የሚጠቀሰውና በ5 ሺህ 250 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለው የናስር ሃይቅም የግብፅ ሌላኛው የቱሪዝም፣ የመስኖና የዓሳ ሃብት ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለችው በጨለማ ወስጥ እየኖረ ካለው ህዝብ ጥቂቱንም ቢሆን ብርሃን እንዲያገኝ በማሰብ ነው።

ኢትዮጵያ 86 በመቶ የአባይ ምንጭ ብትሆንም የስሟ መጠሪያ ከመሆን ባለፈ ሳትጠቀምበት ዘመናት ነጉደዋል።

አባይ “ኤሌክትሪክ እያመነጨልኝ ይፍሰስ” በማለት የዛሬ 10 ዓመት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ብትጀምርም ግብፆች ለማሰናከል ሲያሻቸው በክስ ሲሞቃቸው ደግሞ በማስፈራራት እስካሁንም ዘልቀዋል።