የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት የሚያግዝ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት ተዘጋጀ

112

አሶሳ ፤ መስከረም 05 / 2014( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት የሚያግዝ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት ተዘጋጀ፡፡

የመማሪያ መጽሃፍት የመጀመሪያ ዙር ዝግጅት ማጠቃለያ መርሃ ግብር  በክልሉ ስራ አመራር ማሰልጠኛ ተቋም ተካሂዷል፡፡

በመረሃ ግብሩ ስነ-ስርዓት የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ፤ በትምህርት ጥራት ረገድ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ችግሮቹን  ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የመማሪያ እና ማስተማሪ መጽፍት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ሀገር በቀል እውቀቶች በአዲስ የመማሪያ መጽሃፍት ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሄም  በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት አቅርቦት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ግርማ አሰጌ በበኩላቸው፤  የመማሪያ መጽሃፍት ዝግጅት የበርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻን ጨምሮ በስምንት ቋንቋዎች መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

እስከ አራተኛ ክፍል እየተሰጡ የሚገኙት የማኦ እና ኮሞ ቋንቋዎች በቀጣይ ዓመት  ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

አዲሶቹ መጽሃፍት በ2014 የትምርት ዘመን በክልሉ ከሁሉም ወረዳዎች በተመረጡ 27 አንደኛ፣ መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ስራ ላይ እንደሚውሉ አስታውቀዋል፡፡

ለመጽሃፍት ዝግጅቱ  እስካሁን 48 ሚሊዮን ያህል ብር ወጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አካባቢያዊ እውቀት እና ግብረገብነት ያካተቱት መጽሃፍት በሀገረ አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የግምገማ መስፈርት መሠረት አድርገው የተዘጋጁ መሆኑን  ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም