በርካታ ሱዳናውያን የህዳሴው ግድብ መገንባት ለሱዳን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑ አንድ ጥናት አመላከተ

79

መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ መገንባት ለሱዳን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው በሱዳን ዪኒቨርሲቲ የተጠና አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

በሱዳን አል-ዛኤም አል-አዝሃሪ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢብቲሃል ጋማል ኤል-ዲን The Renaissance Dam: a sustainable conflict or sustainable development በሚል ርዕስ ጥናት በማድረግ ውጤቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚህ ጥናት ውጤት መሰረት 74 በመቶ የሚሆኑት ሱዳናውያን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለሱዳን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣ እናምናለን የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተመላክቷል፡፡

የጥናቱ ዋና ጥያቄ የነበረው የህዳሴ ግድቡ መገንባት ለሱዳን የሚሰጠው ጥቅም እና ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ምንድን ነው የሚል እንደነበር ፕሮፌሰሯ አስታውቀዋል፡፡

ፕሮፌሰሯ ባከናወኑት ጥናት መሰረት 74 በመቶ የሚሆኑት ሱዳናውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንባት ለሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይል በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት፣ የወንዙን የውሃ ፍሰት በመቆጣጠር ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል፣ ጎርፍን ለመከላከል እና በሮሴሪስ ወንዝ ላይ ያለውን የውሃ ማጠራቀሚያ ደህንነት ማስጠበቅ ያስችላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሌላው በጥናቱ ግኝት መሰረት የህዳሴ ግድቡ ችግር ቢገጥመው በአቅራቢያው የሚገኙ የሱዳን ከተሞች በጎርፍ እንዲጥለቀለቁ ያደርጋል፣ የሱዳንን የውሃ ድርሻ ይቀንሳል እንዲሁም የምርታማነት መጠንን ይቀንሳል ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውም ተጠቅሷል፡፡

ፕሮፌሰሯ ይህን የጥናት ውጤት የቀረቡት የሱዳን አል-ዛኤም አል-አዝሃሪ ዩኒቨርሲቲ እና የሱዳን የዜና አገልግሎት ሱና በትብብር ባዘጋጁት (Renaissance Dam, Opportunities and Risks) በሚል በተዘጋጀ አውደ-ጥናት ላይ ሲሆን ለሱዳን ቀጣይ ልማት ይጠቅማል ያሉትን ምክረ-ሃሳብም አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሰረት ሱዳን ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ እንዲሁም ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ የምትችልበት፣ መልካም ጉርብትናን ታሳቢ ያደረገ  እና ሚዛኑን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ፕሮፌሰሯ ምክረ-ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ስልታዊ ራዕይ እና የጥናት ማዕከል እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የህዳሴ ግድቡ ለሱዳን በሚሰጠው ጥቅም እና በሚያስከትለው ጉዳት ዙሪያ የሚታየውን የግንዛቤ ችግር መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንደሚገባ የአልዛይም አላዝሃሪ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር አል ዋሊድ ሞሃመድ አል አሚን ተናግረዋል፡፡

በአውደ-ጥናቱ ላይም ሶስቱ ሀገራት በህዳሴ ግድብ የውሃ አስተዳደር ዙሪያ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ መቅረቡን የሱዳን የዜና አገልግሎት ሱና ዘግቧል፡፡ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንባት የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የልማት ጥያቄ በመሆኑ ጥቅሙ ለኢትዮጵያ፣ ለጎረቤት ሀገራት፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የሚተርፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም