ህዝቡ የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎችን የጥፋት ሴራ ለመቀልበስ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን እንዲሰለፍ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎችን የጥፋት ሴራ ለመቀልበስ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን እንዲሰለፍ ተጠየቀ
ጋምቤላ፤ መስከረም 04 /2014 (ኢዜአ) የህወሓትና ሸኔ የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች በጋምቤላ ክልል ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩትን የጥፋት ሴራ ለመቀልበስ ህዝብ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን እንዲሰለፍ ተጠየቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ የክልሉን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክተው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሽብር ቡድኖቹ ተለላኪዎች በክልሉ ግጭት በመፍጠር ሰላም ለማደፍረስ እየሰሩ ነው።
የህወሓት የሽብር ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት የለመደውን ህዝቦችን የማጋጨት ሴራ ለመድገም ሰሞኑን በተላላኪዎቹ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በዘመን መለወጫ በዓል ዕለት የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች በጋምቤላ ከተማ ግጭት ለማስነሳት ባደረጉት ሙከራ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ጠቁመዋል።
"በዕለቱ በመዝናናት ላይ የነበሩ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ከፈጠሩት አለመግባባት ጋር ተያይዞ በሰባት ሰዎች ላይ የደረሰውን ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ የብሔር መልክ ለማስያዝና የጸጥታ ችግሩ እንዲሰፋ ያደረጉት ሙከራ እንዲከሽፍ ተደርጓል" ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ዘጠኝ ግለሰቦች በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርምራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ኮሚሽነር አቡላ አመልክተዋል።
የክልሉ ፖሊስ ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎችን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመግታት የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች የጥፋት ተልኮ ለማምከን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፈው ሳምንት 19 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን በመጥቀስ።
የሽብር ቡድኖችን ተላላኪዎች የጥፋት ሴራ ለመቀልበስ ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ የድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጠይቀዋል።