ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች የመኖሪያ መንደር ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች የመኖሪያ መንደር ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ
ሀዋሳ ፤ መስከረም 4/2014 (ኢዜአ) ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ከ600 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመኖሪያ መንደር ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ስነ-ስርዓት ላይ ግንባታውን የሚያካሂደው ኮርነር ስቶን ዴቨሎፕሜንት ግሩፕ ካምፓኒ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ሲራክ አምባዬ እንዳሉት፤ ካምፓኒው በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ትኩረት አድርጎ ይሰራል።
ከ600 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚገነባው የሰራተኞች የመኖሪያ መንደር በ18 ወራት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸው፤ ይህም ከ6 ሺህ 500 በላይ ሰራተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
13 ባለሶስትና ባለአራት ወለል ህንጻዎች የሚያካትተው ግንባታው በ22 ሺህ ካሬ ቦታ ላይ እንደሚያርፍ አመልክተው፤ ባንክ ፣ሱቆችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያካተተ ነው ያሉት።
በግንባታው ከ420 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው፤ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለሀብቶችን ለመሳብ እየተገነቡ ከሚገኙ ፓርኮች 13ቱ በማምረት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ፓርኮች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ፓርኮቹ ለማምረት ከሚፈልጉት የስራ ሰዓት፣ ውጤታማነት፣ የምርት ጥራት አንጻር የሰራተኞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ፈተና መሆኑን አሰረድተዋል።
ችግሩን በተቀናጀ መልኩ በማቃለል ፓርኮቹ የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ኮሚሽኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በፓርኮች አካባቢ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አስገዶም ናቸው።
በዚህም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኞች መኖሪያ መንደር ግንባታ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቂ ክትትል በማድረግ ከዚህ በሚገኘው ልምድ በመነሳት ወደ ሌሎች እንደሚሰፋፋ ነው ያስረዱት።
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው፤ የመኖሪያ ቤት ግንባታው ሰራተኞች ገቢያቸውን የሚመጥን ቤት ለማግኘት ከፓርኩ እስከ 10 ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሚመጡ በመሆናቸው በስራ ላይ ያሳድር የነበረውን ጫና እንደሚያቃልል ተናግረዋል።
የመኖሪያ መንደር ግንባታው ለሰራተኛውም ሆነ ለፓርኩ አስተዳደር እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከፓርኩ ሰራተኞች መካከል ወጣት ሊኒ አዱኛ ከተቀጠረች አምስት ዓመት መቆየቷን ገልጻ ከምታገኘው ገቢ አንጻር የመኖሪያ ቤት ዋጋ ፈተና ሆኖባት እንደቆየች ተናግራለች።
ከዚህ የተነሳ አማራጭ ፍለጋ ከተማው ወጣ ባለ አካባቢዎች ቤት ለመከራየት እየተገደዱ በመመላለስ የሚጠፋው ጊዜ በስራቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ጠቁማለች።
የመኖሪያ ቤት እንዲመቻችላቸው ሲያነሱት የነበር ጥያቄ ምላሽ እየገኘ በመሆኑ ችግራቸውም በዚሁ ይቃለላል ብሎ እንደሚጠብቁ ገልጻለች።