ቀጥታ፡

የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዋስትና እንዲያስይዙ የሚያስገድድ መመሪያ ወጣ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዋስትና እንዲያስይዙ የሚያስገድድ መመሪያ መውጣቱን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ገለጸ።

መመሪያው እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች በስፖርት ውርርድ መሳታፍ እንደማይችሉም ይከለክላል።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶችን የተመለከተው መመሪያ መሻሻሉን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋረጄ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በመሆኑም አቋማሪ ድርጅቶችን በተጠናከር ህግና ስርዓት ለመምራት ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ ማሻሻል ማስፈለጉንም አንስተዋል።

አዲሱ መመሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ተሞክሮዎች በመቃኘት መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት።

የአስተዳዳሩ ፍቃድና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ደሴ ደጀኔ በበኩላቸው፤ በተሻሻለው መመሪያ መሰረት የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የባንክ ዋስትና ማስያዝ አለባቸው።

በተጨማሪ በስራ ላይ ያሉ የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ፈቃድ ለማደስ በመመሪያው የተቀመጠውን ዋስትና ማስያዝ ይጠበቅባቸውል።

አዲስ ፍቃድ ለማውጣት ከዚህ በፊት ይከፈል የነበረው 400 ብር በመጠኑ እጅግ ከፍ ብሎ ወደ 500 ሺህ ብር ማደጉንም ተናግረዋል።

እንዲሁም ከዚህ በፊት ፍቃድ ለማደስ ይከፈል የነበረው 200 ብር አሁን ላይ ወደ 100 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።


በተጨማሪ የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች በትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት በሚገኙበት 500 ሜትር ዙሪያ ላይ  ቢሮ መክፈት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት እድሜው 18 ዓመት የሆነው ወጣት በውርርዱ መሳተፍ እንደሚችል አስታውሰው፤ በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች በስፖርት ውርርድ ጨዋታዎች መሳተፍ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

የስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች ከፍተኛ የሽልማት መጠን እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ብቻ እንዲሆን በመመሪያው ተካቷል።

በኢትዮጵያ 42 የስፖርት አቋማሪ  ድርጅቶች ያሉ ሲሆን፤ ከ700 በላይ ቅርንጫፍ ከፍተው እየሰሩ ነው።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳዳር በ2013 በጀት ዓመት ከስፖርት አቋማሪ ድርጅቶች 107 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም