የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመድፈር ያሰበውን አሸባሪ ቡድን ለማሳፈርና ለመቅበር ልጆቻችንን ለህልውና ዘመቻው መርቀን ሸኝተናል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመድፈር ያሰበውን አሸባሪ ቡድን ለማሳፈርና ለመቅበር ልጆቻችንን ለህልውና ዘመቻው መርቀን ሸኝተናል
አዳማ ፤መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) የሀገር ሉዓላዊነት እንዲከበርና ዳርድንበሯ እንዲጠበቅ ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ልጆቻችንን መርቀን ሸኝተናል ሲሉ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አባላት ገለፁ።
"ሀገር የአንድ ሰው ሳትሆን የሁላችን ቤት ናት፤ በመሆኑም ሉዓላዊነቷን ለመድፈር ያሰበውን ጠላት ለማሳፈርና አሸባሪውን ለመቅበር ለልጆቻችንን ሳንሰስት መርቀን ሸኝተናል" ሲሉ ነው የህብረቱ አባላት ለኢዜአ የተናገሩት ።
የህብረቱ አባልና የቱለማ ሃዳ ሲንቄ አፀዱ ቶላ "እኛ አቅም ፈቅዶልን ግንባር ድረስ መሄድ ባንችልም የዘማች ልጆችንና ንብረቱን ከመንከባከብ ባለፈ ለመከላከያ ስንቅ እያዘጋጀን ነው "ብለዋል።
አከባቢያቸውና ሀገር ሰላም እንዲሆን አፍራሽ ሃይሎች ወደ ስነልቦናቸው እንዲመለሱ የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ የጠቀሱት ሃደ ሲንቄ አፀዱ፤ በተለይም የሃዳ ሲንቄ ባህላዊ የማስታረቅ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
"ልጆቻችን ጀግኖች ናቸው፤ ጦርነቱን በጥቂት ጊዜ አጠናቀው ሀገሪቷ ወደ ነበረችበት ሰላምና ልማት በቅርቡ እንድትመለስ በአንድነት መረባረብ አለብን " ብለዋል።
"በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጀው አሸባሪው ህወሃት በፊቱንም ለጥቅሙና ለስልጣኑ ሲል ወዳጅ መስሎ በትከሻችን ላይ ለ27 ዓመታት የቆየ ታሪካዊ ጠላት ነው" ያሉት ደግሞ የቀድሞ የቱለማ አባ ገዳና ሃዩ ገዳ ነገሰ ነገዎ ናቸው።
"ጁንታው ራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበና እየጠፋ ነው" ያሉት ሃዩ ገዳ ነገሰ፤ "መንግስት ከአንዴም ሁለቴ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎችን በመላክ ወደ ሰላም እንዲመለሱ ቢጠይቅም ያንን ወደ ጎን በመተው ወደ ጦርነት የገባ በመሆኑ አሁንም በመረጠው መንገድ ጉዳዩ መጠናቀቅ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን የትግራይን ህፃናት ለስልጣኑና ለገንዘቡ ሲል በጦርነት እያስፈጀ ያለ መሆኑን ህዝቡ ማወቅ አለበት ያሉት ሀዩ ገዳ ነገሰ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ "ይህን አረመኔ ለማጥፋት በአንድነት ተነስቷል" ብለዋል።
"ሀብታችንና መሬታችንን ከመዝረፍ አልፎ የኦሮሞን ባህልና እምነት ለማጥፋት ሲሰራ የነበረ የአሸባሪው ቡድን ተግባር በግልፅ በመውጣቱ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም በአንድነት ተነስቶ ሊያስወግዳቸው ተዘጋጅቷል" ሲሉም አመልክተዋል።
በቱለማ አባ ገዳዎች ምክርቤት አባ አለንጋ የሆኑት አባ ገዳ ፍቃዱ አበራ በበኩላቸው "አሸባሪው ቡድን የኦሮሞን ህዝብ ገድሏል፣ ገርፏል፣ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይሆን ጨቁኗል" በማለት፤ "ህዝቡ ዝም ማለቱ ታላቅ ይቅርታ ነው፤ የህዝባችንንም ታላቅነት የሚያሳይ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
"ህዝቡ የሚጠቅመውን ለይቷል፤ ከመንግስት ጎን ሆኖ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በሙሉ አቅሙ እየደገፈ ነው" ያሉት አባ ገዳ ፍቃዱ የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ ማን ሲገድላቸው፣ ሲበድላቸውና ሲያኮላሻቸው እንደነበር ለይተው ያውቃሉ" ሲሉም አመልክተዋል።
"ልጆቻችንን በመደማመጥ በአንድነትና በቁርጠኝነት የአገር መከላከያን በመቀላቀል ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙ መርቀን ሸኝተናቸዋል" ነው ያሉት።
ወጣትነት ሀብት ፣ ዕውቀት፣ ጉልበትና አቅም በመሆኑ ወጣቶች ወጣትነታቸውን ተጠቅመው የሀገራቸውን አንድነት በመጠበቅ መረከብ እንደሚጠበቅባቸውም አባ ገዳ ፍቃዱ መልእክት አስተላልፈዋል።