አዲሱ ዓመት አሸባሪውን ቡድን ወደተመኘው ሲኦል በመላክ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የምንሰራበት ነው

62

መስከረም 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አዲሱ ዓመት አገር ለማፍረስ ተላላኪ ሆኖ የመጣውን የህወሓት ቡድን ወደተመኘው ሲኦል በመመለስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጠንክረን የምንሰራበት ይሆናል" ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ 2013 የውስጥና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈተኑን ጊዜ እንደነበር አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ዲፕሎማሲያዊ አንድነቷ ተጠብቆ እንዳትቀጥል የሚሹ አፍራሽ ኃይሎች በከፈቱት ጦርነት በሰውና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትም ጠቅሰዋል።

"ባንዳው የህወሓት ቡድን" በመሰረተ ልማት፣ በእምነት ተቋማትና በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አብራርተዋል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በኃይማኖት፣ በሃብትና በዕድሜ ሳይከፋፈሉ አገራቸውን ሊያፈርስ የመጣውን ኃይል ለመመከት በአንድነት ቆመዋል ብለዋል።

ባለሀብቱ  ለሃብቱ ሳይሰስት፣ አርሶ አደሩ፣ የከተማ ነዋሪውና ነጋዴው ያለውን በማዋጣት የትም፣ መቼም፣ በምንም ለአገሩ ሉዓላዊነት መዝመት እንደሚችል በተግባር የሚያሳይበት የታሪክ አጋጣሚ መፈጠሩንም ተናግረዋል።

ይህ አንድነት ለውስጥና ለውጭ ጠላቶች በተለይም በልዩነት ላይ ሲሰራ ለኖረው ለአሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ሕልም "ውሃ እንደበላው ተረጋግጧል" ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ።

የተጠናቀቀው ዓመት ኢትዮጵያዊያን ቋንቋ፣ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው አገራቸውን አሳልፈው እንደማይሰጡ ያስመሰከሩበት ዓመት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አዲሱ 2014 ዓ.ም አገር ለማፍረስ ተላላኪ ሆኖ የመጣውን የጁንታውን ቡድን ወደመጣበትና ወደ ተመኘው ሲኦል በመመለስ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንድትሆን ጠንክረን የምንሰራበት ነው ሲሉም አክለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸው ተጠብቆ በዓለም አደባባይ ከፍ ብለው ይታያሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም