ለመዲናዋ ሰላም መጠበቅ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ለመዲናዋ ሰላም መጠበቅ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2013 (ኢዜአ) ለመዲናዋ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ ተመራቂ ወጣቶች ገለጹ።
ኮሌጁ "እኔ የከተማዬ የሰላም ዘብ ነኝ" በሚል መርህ የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቁ ያሰለጠናቸውን 259 ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።
በስነ-ስርአቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ተመራቂዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የገጠማትን አስቸጋሪ ወቅት በድል እንድታልፍ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጣት ኤሊያስ እስጢፋኖስ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ባለሙያ ሲሆን፤ በኮሌጁ ከተመረቁ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።
የቴኳንዶ ስፖርት አካላዊ እንቅስቃሴን በመጠቀም ጥቃትን መከላከል ፤የግድ ሆኖ ከመጣ ደግሞ የማጥቃት ክህሎትን ከመስጠቱ ባሻገር ወጣቶች መልካም ስነ-ምግባር እንዲኖቸው እንደሚያደርግ ተናግሯል።
የቴኳንዶ ስፖርት ከውትድርና ሙያ ጋር ተቀራራቢነት ያለው በመሆኑ በኮሌጁ ያገኘሁት ስልጠና ሀገሬን ይበልጥ እንዳገለግል ያግዘኛል ብሏል።
በተለይም ሀገር ችግር በገጠማት በዚህ ወቅት ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል እድል ማግኘቱ እንዳስደሰተውም ነው የገለጸው።
በበጎ ፍቃድ የጸጥታ ስራ ላይ የምትሳተፈው ወጣት ፍሬህይወት አባተ በበኩሏ፤ ቀደም ሲል ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢዋን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሏን ሚና ስትወጣ መቆየቷን አስታውሳለች።
"በኮሌጁ የወሰድኩት ስልጠና የከተማዬን ብሎም የአካባቢዬን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የበለጠ ተነሳሽነት ፈጥሮልኛል" ነው በማለትም ገልጻለች።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክት ''አዲስ አበባ የእናንተን ድጋፍ በፈለገችበት ወቅት አዎንታዊ ምላሽ ስለሰጣችሁ ጀግኖች ናችሁ፤ ለዚህም ታሪክ አይዘነጋችሁም'' ሲሉ ተመራቂቹን አወድሰዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ከለውጡ በፊት እያሉ እንደሌሉ የበይ ተመልካች ሆነው መቆየታቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ "አዲስ አበባ የእነርሱ፤ እነርሱም የአዲስ አበባ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ" ብለዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአገር ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ የከተማዋ ወጣቶች ለሀገራቸው ያላቸውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ መሆኑንም ነው ምክትል ከንቲባዋ የገለጹት።
የመዲናዋ ወጣቶች ለመከላከያ ሠራዊቱ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ መሆኑንም አብራርተዋል።
ምክትል ከንቲባዋ የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታ ለማስጠበቅ በበጎ ፈቃደኝነት ለተሰማሩ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት አስተዋጽኦ ላበረከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋና አቅርበዋል።
የከንቲባ ጽህፈት ቤት የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው ተመራቂ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በፍቃደኛነት የተመለመሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ የተሟላ የፖሊስ ስልጠና በመውሰዳቸው የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እንደሚሰማሩም ገልጸዋል።
በቀጣይም 27 ሺ 540 ወጣቶችን ለማሰልጠን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ ሺሰማ አብራርተዋል።