ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን የመኽር እርሻው በታቀደው ልክ ተጠናክሮ ቀጥሏል – መምሪያው

189

ጎንደር፣ መስከረም 4/2013 (ኢዜአ) ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በመኽር እርሻው ከ469 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የማእከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ነጋ ይስማው ለኢዜአ እንደገለጹት የህወሃት የሽብር ቡድን የፈፀመውን ወረራ ከመቀልበስ ጎን ለጎን የመኽር ወቅት የሰብል ልማት ስራን በተያዘው እቅድ ልክ ማሳካት ተችሏል፡፡

በምርት ወቅቱ 489ሺ 590 ሄክታር መሬት አርሶ በሰብል ዘር ለመሸፈን ታቅዶ 97 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በምርት ወቅቱ ለምርት ማሳደጊያ ከተሰራጨው ከ435 ሺ ኩንታል በላይ የፋብሪካ ማዳበሪያ ውስጥ 360 ሺ ኩንታሉ ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል ።

አርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እንዲጠቀም በተደረገ ጥረት በምርት ወቅቱ 150 ሺ ሄክታር መሬት በመስመር መዘራቱንና  50ሺ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አሰራር ዘዴ  በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

የአፈር ለምነትን ለማሻሻል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በኩልም አርሶ አደሩ ከ40ሺ ሄክታር በላይ የጥቁር አፈር የእርሻ መሬትን በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ የዝናብ ውሃን በማንጣፈፍ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በምርት ወቅቱ  ለኢንዱስትሪ ግብአት፣ ለወጭ ንግድና ለምግብ የሚውሉ 10 አይነት የሰብል ዝርያዎችን አርሶ አደሩ በስፋት እንዲያመርት በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ እገዛና ክትትል በመደረግ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዞኑ በምርት ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች የህወሃት የሽብር ቡድን ወረራን ለመቀልበስ በግንባር የዘመቱ ሚሊሻዎች ይዞታ የሆኑ ከ3 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ አርሰው በዘር በመሸፈን እየተንከባከቡ መሆናቸው ሀላፊው አሰታውቀዋል ።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የዳስ ድንዛዝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት ማመይ ”የህወሃት የሽብር ቡድን የግብርና ስራችንን ለማስተጓጎል በከፈተው ወረራ ሳልደናገጥ አንድ ሄክታር ማሳዬን አርሼ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን ችያለሁ” ብለዋል፡፡

“በዘንድሮ የክረምት እርሻ የራሴን ብቻ ሳይሆን ግንባር የዘመቱ ሚሊሻዎችን ማሳ ጭምር በማረስና በመዝራት ድጋፍ አድርጌለአሁ” ያሉት ደግሞ  የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት መንግስቴ ናቸው።

በዞኑ በ2012/13 ምርት ዘመን  መኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል ።